ሆሴዕ 2:5-9

ሆሴዕ 2:5-9 NASV

እናታቸው አመንዝራ ናት፤ በውርደትም ፀንሳቸዋለች፤ እርሷም፣ ‘እንጀራዬንና ውሃዬን ይሰጡኛል፤ ሱፌንና የሐር ልብሴን፣ ዘይቴንና መጠጤን ይሰጡኛል፤ ስለዚህ ውሽሞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ’ አለች። በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾኽ እዘጋለሁ፤ መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ ዐጥራለሁ። ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም። ከዚያም እንዲህ ትላለች፤ ‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤ የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’ እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣ ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን፣ ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣ እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። “ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣ አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤ ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣ ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ።