ዘፍጥረት 24:12-27
ዘፍጥረት 24:12-27 NASV
ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጕዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው። እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘ዕንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይሥሐቅ የመረጥሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያላወቃት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች። ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጕድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው። አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር መንገዱን አሳክቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጅቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር። ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣ “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደ ሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት። እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤ ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው። ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።”

