ዘፍጥረት 24:12-27
ዘፍጥረት 24:12-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም አለ፥ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፤ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በውኃው ጕድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዋ ሰዎች ሴቶች ልጆችም ውኃውን ሊቀዱ ይወጣሉ፤ እንስራሽን አዘንብለሽ ውኃ አጠጭኝ የምላት እርስዋም፦ ‘አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ እስኪረኩ አጠጣለሁ’ የምትለኝ ድንግል፥ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ለአብርሃም ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” እንደዚህ በልቡ ያሰበውን መናገሩን ሳይፈጽም እንዲህ ሆነ፦ የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት የሚልካ ልጅ የባቱኤል ሴት ልጅ ርብቃ እነሆ፥ መጣች፥ እንስራዋንም በጫንቃዋ ተሸክማ ነበር። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማታውቅ ድንግል ነበረች። ወደ ውኃው ጕድጓድም ወረደች፤ ውኃም ቀዳች፤ እንስራዋንም ሞልታ ወጣች። ያም ሰው ሊገናኛት ሮጠና፥ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ አጠጪኝ” አላት። እርስዋም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ከጫንቃዋ በእጅዋ አውርዳ እስኪረካ አጠጣችው። እርሱንም ከአጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለችው። ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፤ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች፤ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። ሰውየውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፤ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሰውዬው አንድ አንድ ወቄት የሚመዝን የወርቅ ጉትቻ፥ ለእጆችዋም ዐሥር ወቄት የሚመዝን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፤ ጠርቶም እንዲህ አላት፥ “አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ እንዳለ እስኪ ንገሪኝ፤” አለችውም፥ “እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት የባቱኤል ልጅ ነኝ። በእኛ ዘንድ ለግመሎችህ ሣርና ገለባ የሚበቃ ያህል አለ፤ ማደሪያም አለን።” ሰውየውም ደስ አለው፤ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። እንዲህም አለ፥ “ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ ለእኔም ወደ ጌታዬ ወደ አብርሃም ወንድም ቤት መንገዴን አቀናልኝ።”
ዘፍጥረት 24:12-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጕዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው። እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘ዕንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይሥሐቅ የመረጥሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያላወቃት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች። ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጕድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው። አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር መንገዱን አሳክቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጅቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር። ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣ “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደ ሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት። እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤ ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው። ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።”
ዘፍጥረት 24:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አለ፦ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ እለምንሃለሁ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃውን ሊቀዱ ይመጣሉ፤ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዩ የምላት እርስዋም፦ አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ እርስዋ ለባሪያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ። ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፤ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፤ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊገናኛት ሮጠና፦ ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ አላት። እርስዋም፦ ጌታዬ ሆይ ጠጣ አለችው ፈጥና፥ እንስራዋን በእጅዋ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኍላ፦ ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ አለች። ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጕድጓዱ ሮጠች ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። ሰውዮውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። ግመሎቹም ከጠጡ በኍላ እንዲህ ሆነ ሰውዮው ግማሽ ሳቅል የሚመዘን የወርቅ ቀለበት ለእጆችዋም አሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ እንዲህንም አላት፦ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን? አለችውም፦ እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን። ሰውዮውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔር ሰገደ። እንዲህም አለ፦ ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።
ዘፍጥረት 24:12-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አገልጋዩም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የእኔን ሐሳብ በመፈጸም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥ። እነሆ፥ እኔ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ ከእነርሱም አንድዋን ልጃገረድ ‘እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ’ እላታለሁ፤ ‘አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውሃ ቀድቼ አመጣለሁ’ ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የመረጥካት እርስዋ ትሁን፤ በዚህም ሁኔታ ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት በቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቈንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጒድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄደና “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። እርስዋም “እሺ ጌታዬ ጠጣ” አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። ጠጥቶም ከረካ በኋላ “ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ” አለችው። ወዲያውኑ በእንስራዋ የያዘችውን ውሃ ግመሎቹ በሚጠጡበት ገንዳ ላይ ገልብጣ ግመሎቹ ሁሉ ጠጥተው እስከሚረኩ ድረስ እየተጣደፈች ከጒድጓድ ውሃ መቅዳት ቀጠለች። ሰውየውም እግዚአብሔር የሄደበትን ተልእኮ አቃንቶለት እንደሆን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሁሉ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር። ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው አምስት ግራም ያኽል የሚመዝን የወርቅ ጒትቻ አውጥቶ በጆሮዋ ላይ አደረገላት፤ መቶ ዐሥር ግራም ያኽል የሚመዝን ሁለት የወርቅ አምባሮችንም አውጥቶ በእጆችዋ ላይ አደረገላትና፥ “የማን ልጅ ነሽ? እስቲ እባክሽ ንገሪኝ፤ ለእኔና አብረውኝ ላሉት ሰዎች ማደሪያ የሚሆን ስፍራ በአባትሽ ቤት ይገኛልን?” ብሎ ጠየቃት። እርስዋም “የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ ባቱኤልም ሚልካ ለናኮር የወለደችለት ነው፤ በቤታችን ብዙ ገለባና ድርቆሽ አለ፤ ለእናንተም ማደሪያ ቦታ ይገኛል” አለችው። ሰውየውም በመንበርከክ ለእግዚአብሔር ሰግዶ፥ “ለጌታዬ ያለውን ታማኝነትና ዘለዓለማዊ ፍቅር የጠበቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በቀጥታ መርቶ ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት ያመጣኝ እርሱ ነው” አለ።
ዘፍጥረት 24:12-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አለ፦ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እለምንሃለሁ፥ መንገዴን ዛሬ በፊቴ አቅናልኝ፥ ለጌታዬም ለአብርሃም ምሕረትን አድርግ። እነሆ፥ በዚህ የውኃ ምንጭ አጠገብ እኔ ቆሜአለሁ፥ የዚህችም ከተማ ሴቶች ልጆች ውኃ ሊቀዱ ይመጣሉ፥ ውኃ እጠጣ ዘንድ እንስራሽን አዘንብዪ የምላት እርሷም አንተ ጠጣ፥ ግመሎችህን ደግሞ አጠጣለሁ የምትለኝ ቆንጆ፥ እርሷ ለባርያህ ለይስሐቅ ያዘጋጀሃት ትሁን፥ በዚህም ለጌታዬ ምሕረትን እንዳደረግህ አውቃለሁ።” ይህን መናገሩንም ሳይፈጽም እነሆ፥ ሚልካ የወለደችው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በጫንቃዋ ተሸክማ ወጣች፥ ሚልካም የአብርሃም ወንድም የናኮር ሚስት ናት። ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች፥ ወደ ምንጭም ወረደች እንስራዋንም ሞላች፥ ተመልሳም ወጣች። ሎሌውም ሊያናግራት ሮጠና፦ “ከእንስራሽ ጥቂት ውኃ ታጠጪኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ጠጣ” አለችው፥ ፈጥናም እንስራዋን በእጇ አውርዳ አጠጣችው። እርሱንም ካጠጣች በኋላ፦ “ለግመሎችህ ደግሞ ሁሉም እስኪረኩ ድረስ ውኃ እቀዳለሁ” አለች። ፈጥናም ውኃውን ከእንስራዋ በማጠጫው ውስጥ ገለበጠችው፥ ደግሞም ልትቀዳ ወደ ጉድጓዱ ሮጠች፥ ለግመሎቹም ሁሉ ውኃ ቀዳች። ሰውዬውም ትክ ብሎ ይመለከታት ነበር፥ እግዚአብሔር መንገዱን አቅንቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅም ዝም አለ። ግመሎቹም ከጠጡ በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበት፥ ለእጆችዋም ዐሥር ሰቅል የሚመዘን ጥንድ የወርቅ አምባር አወጣ፥ እንዲህም አላት፦ “አንቺ የማን ልጅ ነሽ? እስኪ ንገሪኝ፥ በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኛልን?” አለችውም፦ “እኔ ሚልካ ለናኮር የወለደችው የባቱኤል ልጅ ነኝ። በእኛ ዘንድ ገለባና ገፈራ የሚበቃ ያህል አለ፥ ለማደሪያም ደግሞ ስፍራ አለን።” ሰውዬውም አጎነበሰ፥ ለእግዚአብሔርም ሰገደ። እንዲህም አለ፦ “ቸርነቱንና እውነቱን ከጌታዬ ያላራቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እኔ በመንገድ ሳለሁ እግዚአብሔር ወደ ጌታዬ ወንድሞች ቤት መራኝ።”