ዘፍጥረት 16:4-16
ዘፍጥረት 16:4-16 NASV
አብራምም ከአጋር ጋራ ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች። ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው። አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደ ሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች። የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር። መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት። እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች። የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለርሷም ተገዥላት” አላት። ደግሞም የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት። የእግዚአብሔርም መልአክ በተጨማሪ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ እግዚአብሔር ችግርሽን ተመልክቷል፤ ስሙን እስማኤል ትዪዋለሽ። እርሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል፤ እጁንም ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ ያነሣል፤ ያገኘውም ሁሉ እጁን ያነሣበታል፤ ከወንድሞቹ ሁሉ ጋራ እንደ ተጣላ ይኖራል።” እርሷም ያናገራትን እግዚአብሔርን፣ “ኤልሮኢ” ብላ ጠራችው፤ ምክንያቱም “የሚያየኝን አሁን አየሁት” ብላ ነበርና። ከዚህ የተነሣ የዚያ ምንጭ ስም፣ “ብኤርላሃይሮኢ” ተብሎ ተጠራ፤ እስካሁንም በቃዴስና በባሬድ መካከል ይገኛል። አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም ስሙን እስማኤል ብሎ ጠራው። አብራም፣ አጋር እስማኤልን በወለደች ጊዜ ዕድሜው 86 ዓመት ነበር።

