ዘፍጥረት 16:4-16
ዘፍጥረት 16:4-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አብራምም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፤ እንደ ፀነሰችም ባየች ጊዜ እመቤቷን ማክበርዋን ተወች። ሦራም አብራምን፥ “ከአንተ የተነሣ እገፋለሁ፤ እኔ አገልጋዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንደ ፀነሰችም ባየች ጊዜ እኔን ማክበርን ተወች፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ” አለችው። አብራምም ሚስቱን ሦራን፥ “እነሆ፥ አገልጋይሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት” አላት። ሦራም አጋርን አሠቃየቻት፤ ከእርስዋም ኰበለለች። የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በሱር በረሃ በመንገድ አገኛት። የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጂያለሽ?” አላት። እርስዋም፥ “እኔ ከእመቤቴ ከሦራ ፊት እኰበልላለሁ” አለች። የእግዚአብሔር መልአክም፥ “ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፤ ከእጅዋም በታች ራስሽን ዝቅ አድርጊ” አላት። እግዚአብሔርም “ከብዛቱ የተነሣ እስከማይቈጠር ድረስ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥” አላት። የእግዚአብሔር መልአክም አላት፥ “እነሆ፥ አንቺ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ይስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፤ እግዚአብሔር ሥቃይሽን ሰምቶአልና። እርሱም የበረሃ ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፤ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል።” አጋርም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ጠራች፤ “አቤቱ የራራህልኝ አንተ ነህ፤ የተገለጠልኝን በፊቴ አይችዋለሁና።” ስለዚህም የዚያን ጕድጓድ ስም “በፊቴ የተገለጠልኝ የእርሱ ጕድጓድ” ብላ ጠራችው፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። አጋርም ተመለሰች። ከዚህም በኋላ አጋር ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የሕፃኑን ስም ይስማኤል ብሎ ጠራው። አጋር ይስማኤልን በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።
ዘፍጥረት 16:4-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አብራምም ከአጋር ጋራ ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች። ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው። አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደ ሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች። የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር። መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት። እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች። የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለርሷም ተገዥላት” አላት። ደግሞም የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት። የእግዚአብሔርም መልአክ በተጨማሪ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ እግዚአብሔር ችግርሽን ተመልክቷል፤ ስሙን እስማኤል ትዪዋለሽ። እርሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል፤ እጁንም ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ ያነሣል፤ ያገኘውም ሁሉ እጁን ያነሣበታል፤ ከወንድሞቹ ሁሉ ጋራ እንደ ተጣላ ይኖራል።” እርሷም ያናገራትን እግዚአብሔርን፣ “ኤልሮኢ” ብላ ጠራችው፤ ምክንያቱም “የሚያየኝን አሁን አየሁት” ብላ ነበርና። ከዚህ የተነሣ የዚያ ምንጭ ስም፣ “ብኤርላሃይሮኢ” ተብሎ ተጠራ፤ እስካሁንም በቃዴስና በባሬድ መካከል ይገኛል። አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም ስሙን እስማኤል ብሎ ጠራው። አብራም፣ አጋር እስማኤልን በወለደች ጊዜ ዕድሜው 86 ዓመት ነበር።
ዘፍጥረት 16:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። ሦራም አብራምን፥ መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፤ እኔ ባሪያዬን በብብትህ ሰጠሁህ፤ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፤ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ፥ መካከል ይፍረስ አለችው። አብራምም ሦራን፥ እነሆ ባሪያሽ በእጅሽ ናት፤ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦርም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች። የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። እርሱም፤ የሦራ ባሪያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ? አላት። እርስዋም፥ እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ አለች። የእግዚአብሔር መልአክም፥ ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ አላት። የእግዚአብሔር መልአክም፥ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት። የእግዚአብሔር መልአክም አላት፥ እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና። እርሱም የበዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፤ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፤ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል። እርስዋም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ስለዚህም የዚያ ጕድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፤ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው። አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ።
ዘፍጥረት 16:4-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አብራም ወደ አጋር ገባ፤ ፀነሰችም፤ አጋር መፅነስዋን ባወቀች ጊዜ በእመቤትዋ ላይ ኮራች፤ ናቀቻትም። ሣራይም አብራምን “የደረሰብኝ በደል በአንተ ላይ ይሁን፤ እርስዋን ለአንተ የሰጠሁህ እኔ ራሴ ነኝ፤ እርስዋ ግን መፅነስዋን ካወቀችበት ጊዜ አንሥቶ እኔን መናቅ ጀምራለች፤ አሁንም ከእኔና ከአንተ ጥፋተኛው ማን እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይፍረድ!” አለችው። አብራምም “መልካም ነው፤ እርስዋ የአንቺ አገልጋይ ስለ ሆነች በቊጥጥርሽ ሥር ናት፤ የፈለግሺውን ነገር አድርጊ” አላት። ከዚህ በኋላ ሣራይ አጋርን እጅግ ስላሠቃየቻት አጋር ከቤት ወጥታ ኰበለለች። የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በበረሓ በሚገኘው በአንድ ምንጭ አጠገብ አገኛት፤ ይህም ምንጭ ወደ ሹር በሚወስደው መንገድ ላይ ነበር። መልአኩም “የሣራይ አገልጋይ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጂአለሽ?” አላት። እርስዋም “እኔ ከእመቤቴ ከሣራይ ሸሽቼ ነው” አለችው። መልአኩም “ወደ እመቤትሽ ተመለሽና አገልግያት” አላት። ደግሞም እንዲህ አላት፤ “ማንም ሊቈጥረው እስከማይችል ድረስ ዘርሽን አበዛዋለሁ፤ እነሆ፥ ፀንሰሻል፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ እግዚአብሔር የሐዘን ለቅሶሽን ስለ ሰማልሽ ስሙን እስማኤል ትይዋለሽ። ነገር ግን እንደ ሜዳ አህያ ይሆናል፤ ሰውን ሁሉ ይቃወማል፤ ሰዎችም እርሱን ይቃወሙታል፤ ዘመዶቹን በመጥላት ተለይቶ ይኖራል።” አጋርም “በእርግጥ የሚያየኝን እግዚአብሔርን በዐይኔ አይቼ በሕይወት ኖርሁን?” በማለት ያነጋገራትን ጌታ “ኤልሮኢ” አለችው፤ ትርጒሙም “የሚያየኝ አምላክ” ማለት ነው። ስለዚህ ሰዎች በቃዴስና በባሬድ መካከል የሚገኘውን የውሃ ጒድጓድ “ብኤር ላሐይ ሮኢ” ብለው ይጠሩታል፤ ትርጒሙም “ሕያው የሆነውና የሚያየኝ አምላኬ ጒድጓድ” ማለት ነው። አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ እርስዋ የወለደችለትንም ልጅ “እስማኤል” ብሎ ስም አወጣለት፤ አብራም በዚያን ጊዜ 86 ዓመት ሆኖት ነበር።
ዘፍጥረት 16:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም ወደ አጋር ገባ፥ አረገዘችም፥ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እመቤትዋን በዓይንዋ አቃለለች። ሦራም አብራምን፦ መገፋቴ በአንተ ላይ ይሁን፥ እኔ ባርያዬን በጉያህ ሰጠሁህ፥ እንዳረገዘችም ባየች ጊዜ እኔን በዓይንዋ አቃለለችኝ፥ እግዚአብሔር በእኔና በአንተ መካከል ይፍረድ አለችው። አብራምም ሣራን፦ እነሆ ባርያሽ በእጅሽ ናት፥ እንደ ወደድሽ አድርጊባት አላት። ሦራም ባሠቀየቻት ጊዜ አጋር ከፊትዋ ኮበለለች። የእግዚአብሔር መልአክም በውኃ ምንጭ አጠገብ በበረሀ አገኛት፥ ምንጩም ወደ ሱር በምትወስደው መንገድ አጠገብ ነው። እርሱም፦ “የሦራ ባርያ አጋር ሆይ፥ ከወዴት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት። እርሷም፦ “እኔ ከእመቤቴ ከሦራ የኮበለልሁ ነኝ” አለች። የእግዚአብሔር መልአክም፦ “ወደ እመቤትሽ ተመለሺ፥ ከእጅዋም በታች ሆነሽ ተገዥ” አላት። የእግዚአብሔር መልአክም፦ ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፥ ከብዛቱም የተነሣ አይቆጠርም አላት። የእግዚአብሔር መልአክም አላት፦ እነሆ አንቺ ፀንሰሻል፥ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም እስማኤል ብለሽ ትጠሪዋለሽ፥ እግዚአብሔር መቸገርሽን ሰምቶአልና። እርሱም የሜዳ አህያን የሚመስል ሰው ይሆናል፥ እጁ በሁሉ ላይ ይሆናል፥ የሁሉም እጅ ደግሞ በእርሱ ላይ ይሆናል፥ እርሱም በወንድሞቹ ሁሉ ፊት ይኖራል። እርሷም ይናገራት የነበረውን የእግዚአብሔርን ስም ኤልሮኢ ብላ ጠራች፥ የሚያየኝን በውኑ እዚህ ደግሞ አየሁትን? ብላለችና። ስለዚህም የዚያ ጉድጓድ ስም ብኤርለሃይሮኢ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በቃዴስና በባሬድ መካከል ነው። አጋርም ለአብራም ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ አብራምም አጋር የወለደችለትን የልጁን ስም እስማኤል ብሎ ጠራው። አጋር እስማኤልን ለአብራም በወለደችለት ጊዜ አብራም የሰማንያ ስድስት ዓመት ሰው ነበረ።