ዘፀአት 17:1-16
ዘፀአት 17:1-16 NASV
መላው የእስራኤል ማኅበር ከሲና ምድረ በዳ ተነሥቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጕዞ በራፊዲም ሰፈረ፤ ነገር ግን ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ አልነበረም። ስለዚህ፣ “የምንጠጣውን ውሃ ስጠን” በማለት ሙሴን ተጣሉት። ሙሴም፣ “እኔን ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አለ። ነገር ግን ሕዝቡ በዚያ ተጠምተው ስለ ነበር፣ በሙሴ ላይ አጕረመረሙ። እነርሱም፣ “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውሃ ጥም እንድናልቅ፣ ከግብጽ ለምን አወጣኸን?” አሉት። ከዚያም ሙሴ፤ “በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ መለሰለት፤ “ከሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ከእስራኤል አለቆች አንዳንዶቹን እንዲሁም አባይን የመታህባትን በትር ያዝና ሂድ። ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ። ስፍራውንም ማሳህና መሪባ ብሎ ጠራው፤ እስራኤላውያን ጠብ ፈጥረው፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው ወይስ አይደለም” በማለት እግዚአብሔርን ተፈታትነዋልና። አማሌቃውያን መጥተው እስራኤላውያንን ራፊዲም ላይ ወጉ፤ ሙሴም ኢያሱን፣ “ከሰዎቻችን አንዳንዶቹን ምረጥና አማሌቃውያንን ለመውጋት ውጣ፤ በነገው ዕለት የእግዚአብሔርን በትር በእጆቼ ይዤ በኰረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ።” ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋራ ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ። ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር። የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቈዩ ነው። ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ። ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈጽሜ እደመስሳለሁ” አለው። ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር ዐርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው። “እጆች ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ተዘርግተዋልና፤ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።

