መክብብ 6:1-12

መክብብ 6:1-12 NASV

ከፀሓይ በታች ሌላ ክፉ ነገር አየሁ፤ እርሱም ለሰዎች እጅግ የሚከብድ ነው፤ ሰው ልቡ የሚሻውን እንዳያጣ፣ አምላክ ባለጠግነትን፣ ሀብትንና ክብርን ይሰጠዋል፤ አምላክ ግን እንዲደሰትበት ሥልጣን አልሰጠውም፤ ይልቁን ባዕድ ይደሰትበታል። ይህም ከንቱ፣ እጅግም ክፉ ነገር ነው። አንድ ሰው መቶ ልጅ ሊኖረውና ብዙ ዓመት ሊኖር ይችላል፤ ምንም ያህል ይኑር፣ በሀብቱ ደስ ካልተሠኘበትና በአግባብ ካልተቀበረ፣ ከርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል እላለሁ፤ ምክንያቱም በከንቱ ይመጣል፤ በጨለማም ይሄዳል፤ ስሙም በጨለማ ተሸፍኗል። ፀሓይን ባያይና ምንም ነገር ባያውቅ እንኳ፣ እርሱ ከዚያ ሰው ይልቅ ዕረፍት አለው፤ ሁለት ጊዜ ሺሕ ዓመት ቢኖር፣ ነገር ግን በሀብቱ ደስ ባይሠኝበት፣ ሁሉ ወደዚያ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? የሰው ጥረት ሁሉ ለአፉ ነው፤ ፍላጎቱ ግን ፈጽሞ አይረካም። ጠቢብ ከሞኝ ይልቅ ምን ብልጫ አለው? ድኻስ በሌሎች ፊት እንዴት እንደሚኖር በማወቁ፣ ትርፉ ምንድን ነው? በምኞት ከመቅበዝበዝ፣ በዐይን ማየት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። አሁን ያለው ሁሉ አስቀድሞ ስም የተሰጠው ነው፤ ሰው የሚሆነውም አስቀድሞ የታወቀ ነው፤ ከራሱ ይልቅ ከሚበረታ ጋራ፣ ማንም አይታገልም። ቃል በበዛ ቍጥር፤ ከንቱነት ይበዛል፤ ይህ ታዲያ ለሰው ምን ይጠቅማል? ሰው በሕይወት ሳለ፣ እንደ ጥላ በሚያልፉት ጥቂትና ከንቱ በሆኑት ቀኖቹ፣ ለሰው መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ከሄደ በኋላስ ከፀሓይ በታች የሚሆነውን ማን ሊነግረው ይችላል?