መክብብ 6:1-12
መክብብ 6:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የበዛ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለሰውነቱ የከለከላት የለም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ ብዙ ዘመንም በሕይወት ቢኖር፥ ዕድሜውም ብዙ ዓመት ቢሆን፥ ነገር ግን ነፍሱ መልካምን ባትጠግብ፥ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ፥ “ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል” አልሁ። በከንቱ መጥቶአል፥ በጨለማም ይሄዳል፥ ስሙ በጨለማ ይሸፈናልና። ደግሞም ፀሐይን አላየም፥ አላወቀምም፤ ስለዚህ ከዚያ ይልቅ ለዚህ ዕረፍት አለው። ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር፥ መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? የሰው ድካም ሁሉ በአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። ከአላዋቂ ይልቅ ለጠቢብ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድን ለሚያውቅ ለድሃ ጥቅሙ ምንድር ነው? በዐይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፥ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የሆነው ሁሉ እነሆ፥ ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፤ ከእርሱም ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም። ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና፥ ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማን ነው? ወይስ ለሰው ከፀሓይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?
መክብብ 6:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከፀሓይ በታች ሌላ ክፉ ነገር አየሁ፤ እርሱም ለሰዎች እጅግ የሚከብድ ነው፤ ሰው ልቡ የሚሻውን እንዳያጣ፣ አምላክ ባለጠግነትን፣ ሀብትንና ክብርን ይሰጠዋል፤ አምላክ ግን እንዲደሰትበት ሥልጣን አልሰጠውም፤ ይልቁን ባዕድ ይደሰትበታል። ይህም ከንቱ፣ እጅግም ክፉ ነገር ነው። አንድ ሰው መቶ ልጅ ሊኖረውና ብዙ ዓመት ሊኖር ይችላል፤ ምንም ያህል ይኑር፣ በሀብቱ ደስ ካልተሠኘበትና በአግባብ ካልተቀበረ፣ ከርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል እላለሁ፤ ምክንያቱም በከንቱ ይመጣል፤ በጨለማም ይሄዳል፤ ስሙም በጨለማ ተሸፍኗል። ፀሓይን ባያይና ምንም ነገር ባያውቅ እንኳ፣ እርሱ ከዚያ ሰው ይልቅ ዕረፍት አለው፤ ሁለት ጊዜ ሺሕ ዓመት ቢኖር፣ ነገር ግን በሀብቱ ደስ ባይሠኝበት፣ ሁሉ ወደዚያ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? የሰው ጥረት ሁሉ ለአፉ ነው፤ ፍላጎቱ ግን ፈጽሞ አይረካም። ጠቢብ ከሞኝ ይልቅ ምን ብልጫ አለው? ድኻስ በሌሎች ፊት እንዴት እንደሚኖር በማወቁ፣ ትርፉ ምንድን ነው? በምኞት ከመቅበዝበዝ፣ በዐይን ማየት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። አሁን ያለው ሁሉ አስቀድሞ ስም የተሰጠው ነው፤ ሰው የሚሆነውም አስቀድሞ የታወቀ ነው፤ ከራሱ ይልቅ ከሚበረታ ጋራ፣ ማንም አይታገልም። ቃል በበዛ ቍጥር፤ ከንቱነት ይበዛል፤ ይህ ታዲያ ለሰው ምን ይጠቅማል? ሰው በሕይወት ሳለ፣ እንደ ጥላ በሚያልፉት ጥቂትና ከንቱ በሆኑት ቀኖቹ፣ ለሰው መልካም የሆነውን የሚያውቅ ማን ነው? እርሱ ከሄደ በኋላስ ከፀሓይ በታች የሚሆነውን ማን ሊነግረው ይችላል?
መክብብ 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፥ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፥ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነፍሱም መልካምን ባትጠግብ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ፦ ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። በከንቱ መጥቶአል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፥ ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፥ ለዚህም ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን? የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። ከሰነፍ ይልቅ ለጥበበኛ ጥቅም ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድ ለሚያውቅ ለድሀ ጥቅሙ ምንድር ነው? በዓይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የሆነውም ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፥ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም። ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?
መክብብ 6:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚህ ዓለም በሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ እጅግ የከፋ ነገር ተመለከትኩ። እግዚአብሔር ለሰው ምድራዊ ሀብትንና ብልጽግናን ክብርንም ሁሉ ይሰጠዋል፤ ከሚያስፈልገውም ነገር ሁሉ ምንም አያጐድልበትም፤ ይሁን እንጂ በሚሰጠው ሀብት ሁሉ አይደሰትበትም፤ ይልቁንም እርሱ ደክሞ ያፈራውን ሌላ ሰው ይደሰትበታል። ይህም ከንቱና እጅግ የከፋ በደል ነው። እንግዲህ፥ አንድ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ ረጅም ዕድሜ አግኝቶ ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖርም፥ እንዲደሰትበት ከሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ድርሻውን ሳያገኝ ቀርቶ በመጨረሻም በክብር ለመቀበር ሳይበቃ ቢቀር፥ እኔ ስለ እርሱ አዝናለሁ፤ ከእንደዚህ ያለውም ሰው ይልቅ በእናቱ ማሕፀን ሞቶ የተወለደ ጭንጋፍ ይሻላል አልኩ። ያ ጭንጋፍ ተረስቶ ወደሚቀርበት ጨለማ ስለሚወሰድ ቀድሞውኑ ሳይወለድ ቢቀር በተሻለው ነበር። እርሱ የፀሐይን ብርሃን ሳያይ የሕይወትንም ምንነት ሳያውቅ አንድ ጊዜ ዐርፎአል። ስለዚህ ሁለት ሺህ ዓመት ያለ ደስታ ቢኖር ጥቅሙ ምንድን ነው? ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የሚሄዱት ወደ አንድ ተመሳሳይ ስፍራ ነው። ሰው በሥራ መድከሙ የሚበላውን ነገር ለማግኘት ነበር፤ ይሁን እንጂ “በቃኝ!” ማለት አያውቅም። ታዲያ፥ ጥበበኛ ሰው ከሞኝ የሚሻልበት ምን ነገር አለ? ለድኻስ ሕይወትን ለመምራት መቻሉ የሚያተርፍለት ጥቅም ምንድን ነው? ለምኞት ከመገዛት ይልቅ ባለ ነገር መርካት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱና ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው። ያለ ነገር ሁሉ ስም ተሰጥቶታል፤ የሰዎችም ማንነት ታውቆአል፤ ከእነርሱ በላይ ብርቱ ከሆነው ጋር መቋቋም አይችሉም። ብዙ በተናገርን መጠን ቁምነገሩ ያነሰ ነው፤ ስለዚህ የመናገር ጥቅሙ ምንድን ነው? ከንቱ ሆኖ እንደ ጥላ በሚያልፍ ዘመኑ ለሰው የሚበጀውን ነገር የሚያውቅ ማን ነው? ወይስ ከሞተ በኋላ በዚህ ዓለም ምን እንደሚሆን ለሰው ማን ሊነግረው ይችላል?
መክብብ 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የከበደ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ሀብትን፥ ንብረትንና ክብርን ሰጠው፥ ከወደደውም ነገር ሁሉ ለነፍሱ አልጐደለውም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር ሥልጣን አልሰጠውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ እጅግ ዘመንም በሕይወት ቢኖር፥ ዕድሜውም እጅግ ዓመት ቢሆን፥ ነገር ግን ነፍሱ መልካምን ነገር ባትጠግብ፥ መቃብርንም ባያገኝ፥ ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል አልሁ። በከንቱ መጥቷል በጨለማ ይሄዳል ስሙም በጨለማ ይሸፈናል፥ ደግሞም ፀሐይን አላየውም አላወቀውምም፥ ቢሆንም እርሱ ከዚያ ይልቅ ዕረፍት አለው። ለሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር፥ ነገር ግን መልካምን ባያይ፥ ሁሉም ወደ አንድ ስፍራ ይሄድ የለምን? የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። ጥበበኛ ከአላዋቂ ምን የተሻለ ጥቅም ያገኛል? ሕይወትን መምራት የሚያውቅ ድሀስ ምን ይጠቀማል? በዐይን ማየት በምኞት ከመቅበዝበዝ ይሻላል፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የሆነው ነገር በሙሉ ስሙ አስቀድሞ ተጠርቷል፥ ሰውም ማን እንደሆነ ታወቀ፥ ከእርሱ ከሚበረታው ጋር መፋረድ አይችልም። ንግግር በበዛ መጠን፥ ከንቱነትም ይበዛል፤ ለሰውስ ምን ይጠቅመዋል? ሰው በከንቱ የሕይወቱ ቀናት ቍጥር ና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ለሰው ማን ይነግረዋል?