አሞጽ 7:1-9

አሞጽ 7:1-9 NASV

ጌታ እግዚአብሔር ይህን አሳየኝ፤ የንጉሡ የመኸር እህል ከተሰበሰበ በኋላ ገቦው መብቀል በጀመረ ጊዜ፣ እርሱ የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ። አንበጦች የምድሩን ሣር ግጠው ከጨረሱት በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ። እግዚአብሔርም “ይህ አይፈጸምም” አለ። ጌታ እግዚአብሔር ይህንም አሳየኝ፤ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ፤ ምድሪቱንም በላ። ከዚያም በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንድትተወው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ጌታ እግዚአብሔር፣ “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለ። ይህንም ደግሞ አሳየኝ፤ ጌታ በእጁ ቱንቢ ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር አጠገብ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔር፣ “አሞጽ፣ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፣ “ቱንቢ” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ አልምራቸውም። “የይሥሐቅ ማምለኪያ ኰረብቶች ባድማ ይሆናሉ፤ የእስራኤል መቅደሶች ይፈርሳሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፌ እነሣለሁ።”