አሞጽ 7:1-9
አሞጽ 7:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም ከምሥራቅ አንበጣ ይመጣል፤ አንዱም ኵብኵባ ንጉሡ ጎግ ነበረ። የምድሩንም ሣር በልቶ ይጨርሳል፤ እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብን ማን ያነሣዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ አይሆንም፤” ይላል እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም ጌታ እግዚአብሔር ለመፍረድ በቃሉ እሳትን ጠራ፤ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብን ማን ያነሣዋል? ጥቂት ነውና” አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ራራ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም አንድ ሰው በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር፤ በእጁም ቱንቢ ነበር። እግዚአብሔርም፥ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፥ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም፥ “እነሆ! በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ ይቅር አልላቸውም። መሳቂያ የሆኑ የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ” አለ።
አሞጽ 7:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጌታ እግዚአብሔር ይህን አሳየኝ፤ የንጉሡ የመኸር እህል ከተሰበሰበ በኋላ ገቦው መብቀል በጀመረ ጊዜ፣ እርሱ የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ። አንበጦች የምድሩን ሣር ግጠው ከጨረሱት በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ። እግዚአብሔርም “ይህ አይፈጸምም” አለ። ጌታ እግዚአብሔር ይህንም አሳየኝ፤ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ሊፈርድ ተዘጋጀ፤ እሳቱም ታላቁን ጥልቅ አደረቀ፤ ምድሪቱንም በላ። ከዚያም በኋላ፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንድትተወው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ይችላል? ታናሽ ነው እኮ!” አልሁ። እግዚአብሔር ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ ጌታ እግዚአብሔር፣ “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለ። ይህንም ደግሞ አሳየኝ፤ ጌታ በእጁ ቱንቢ ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር አጠገብ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔር፣ “አሞጽ፣ የምታየው ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም፣ “ቱንቢ” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲያ አልምራቸውም። “የይሥሐቅ ማምለኪያ ኰረብቶች ባድማ ይሆናሉ፤ የእስራኤል መቅደሶች ይፈርሳሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፌ እነሣለሁ።”
አሞጽ 7:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ የኋለኛው ሣር በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፥ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ የበቀለ የገቦ ነበረ። የምድሩንም ሣር በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ አይሆንም፥ ይላል እግዚአብሔር። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፥ እርስዋም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንድትተው እለምንሃለሁ፥ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል? አልሁ። እግዚአብሔርም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፥ ይህ ደግሞ አይሆንም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፥ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም፦ አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም፦ ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም፦ እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፥ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፥ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ።
አሞጽ 7:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጌታ እግዚአብሔር ይህን ራእይ አሳየኝ፤ እነሆ የንጉሡ የመከር እህል ከታጨደ በኋላ እንደገና ገቦ ሆኖ በበቀለው እህል ላይ እግዚአብሔር የአንበጣ መንጋ እንዲፈለፈል አደረገ፤ አንበጦቹም የምድሩን ልምላሜ ሁሉ ግጠው እንደ በሉት ባየሁ ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እባክህ የሕዝብህን በደል ይቅር በል! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም ስለሌላቸው እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?” እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህ ያየኸው ነገር አይፈጸምም!” አለኝ። ጌታ እግዚአብሔር የገለጠልኝ ሌላውም ራእይ ይህ ነው፤ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር የእሳት ቅጣት ፍርድ አስተላለፈ፤ እሳቱም ባሕሩን በልቶ ካደረቀው በኋላ ምድርን ማቃጠል ጀመረ። በዚያን ጊዜ እኔ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ እሳቱ እንዲቆም አድርግ! ሕዝብህ እስራኤል ዐቅም የሌላቸው ስለ ሆኑ እንዴት ተቋቊመው መኖር ይችላሉ?” እግዚአብሔርም ራርቶላቸው “ይህም ደግሞ አይፈጸምም” አለኝ። እግዚአብሔር ሌላ ራእይ ገለጠልኝ፤ እነሆ እግዚአብሔር በቱምቢ ተስተካክሎ በተሠራ ቅጽር አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ በእጁም ቱምቢ ይዞ ነበር፤ እርሱም “አሞጽ ሆይ! የምታየው ነገር ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “ቱምቢ ነው” አልኩ። ጌታም እንዲህ አለኝ፦ “በቱምቢ ተስተካክሎ እንዳልተሠራ ቅጽር ሕዝቤ እስራኤል ጠማሞች ሆነው ስለ ተገኙ ይህ ቱምቢ የእስራኤልን ጠማማነት ማሳያ ምሳሌ ነው፤ ሳልቀጣቸውም አላልፍም። የይስሐቅና የልጅ ልጆቹ ከፍተኛ የመስገጃ ቦታዎች ይፈራርሳሉ፤ የእስራኤልም የተቀደሱ ቦታዎች ፈራርሰው ወና ይሆናሉ፤ የኢዮርብዓምን መንግሥት ፈጽሞ አጠፋለሁ።”
አሞጽ 7:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ መከር ካለፈ በኋላ ያለው እህል በሚበቅልበት መጀመሪያ ላይ አንበጣን ፈጠረ፤ እነሆም፥ ከንጉሡ አጨዳ በኋላ ማንም ሰው ሳይዘራው የበቀለ ነበረ። የምድሩንም እጽዋት በልተው ከጨረሱ በኋላ፥ እኔ፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር እንድትል እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ አይሆንም፥” ይላል ጌታ። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ እግዚአብሔር በእሳት ለመፍረድ ጠራ፤ እርሷም ታላቁን ቀላይና ምድርን በላች። እኔም፦ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እንድትተው እለምንሃለሁ፤ ያዕቆብ ታናሽ ነውና እንዴት ይቆማል?” አልሁ። ጌታም ስለዚህ ነገር ተጸጸተ፤ “ይህ ደግሞ አይሆንም፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። ጌታም፦ “አሞጽ ሆይ! የምታየው ምንድነው?” አለኝ። እኔም፦ “ቱንቢ ነው” አልሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ “እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ እዘረጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ዳግመኛ አላልፋቸውም፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ።”