1 ዜና መዋዕል 16:1-36

1 ዜና መዋዕል 16:1-36 NASV

ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕትም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ፣ ሕዝቡን በእግዚአብሔር ስም ባረከ። ከዚያም ለእስራኤል ሁሉ ለወንዱም ለሴቱም አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ። በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እንዲያገለግሉና ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ልመና፣ ምስጋናና ውዳሴ እንዲያቀርቡ ከሌዋውያን ሰዎች ሾመ፤ አለቃው አሳፍ ነበረ፤ ከርሱ ቀጥሎ ዘካርያስ ሁለተኛ ሆኖ ተሾመ፤ ከዚያም ይዒኤል፣ ሰሚራሞት፣ ይሒኤል፣ መቲትያ፣ ኤልያብ፣ በናያስ፣ አቢዳራ፣ ይዒኤል ተሾሙ፤ እነርሱም በመሰንቆና በበገና ይዘምሩ ነበር፤ አሳፍ ደግሞ ጸናጽል የሚጸነጽል ሆኖ ተመደበ። እንዲሁም ካህናቱ በናያስና የሕዚኤል ዘወትር በእግዚአብሔር የኪዳኑ ታቦት ፊት መለከት እንዲነፉ ተመደቡ። በዚያም ቀን ዳዊት በመጀመሪያ ለአሳፍና ለሥራ ጓደኞቹ ይህን የእግዚአብሔር ምስጋና መዝሙር ሰጠ፤ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ሥራውንም በሕዝቦች መካከል አሳውቁ። ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤ ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ፤ በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ። እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤ ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ። ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤ እናንተ የባሪያው የእስራኤል ዘሮች፣ እናንተ የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች። እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፤ ኪዳኑን ለዘላለም፣ ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል። ከአብርሃም ጋራ የገባውን ቃል ኪዳን፣ ለይሥሐቅም የማለውን መሐላ። ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፤ ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤ እንዲህ ሲል፣ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣ የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ” ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣ በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣ ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣ ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው ተንከራተቱ። ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤ እንዲህ ሲል፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤ በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።” ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ። ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤ ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ ነውና፤ ውዳሴውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ ይገባዋል። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ። የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ። ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤ በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ። ምድር ሁሉ በፊቱ ትንቀጥቀጥ፤ ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም። ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድርም ሐሤት ታድርግ፤ በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ። ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ያስተጋባ፤ ሜዳዎችና በርሷ ላይ ያሉ ሁሉ በደስታ ይዘምራሉ። ያን ጊዜ የዱር ዛፎች በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤ በደስታ ይዘምራሉ፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና። ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። “የመዳናችን አምላክ ሆይ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤ ከአሕዛብም መካከል ታደገን” ብላችሁ ጩኹ። ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ፣ “አሜን፤ እግዚአብሔር ይመስገን” አሉ።