ሮሜ 9:10-15
ሮሜ 9:10-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ለእርስዋ ብቻ አይደለም፤ ርብቃም ለአባታችን ለይስሐቅ መንታ በፀነሰች ጊዜ፥ ሳይወለዱ፥ ክፉና መልካም ሥራም ሳይሠሩ የእግዚአብሔር መምረጡ በምን እንደ ሆነ ይታወቅ ዘንድ፥ እርሱ የጠራው ነው እንጂ ሰው በሥራው የሚመረጥ አንዳይደለም ያውቁ ዘንድ፥ ለርብቃ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል” አላት። “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአልና። እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያደላልን? አያደላም። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ይቅር የምለውንም ይቅር እለዋለሁ።”
ሮሜ 9:10-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህም ብቻ ሳይሆን፣ የርብቃ ልጆች አንድ አባት አላቸው፤ እርሱም አባታችን ይሥሐቅ ነው። መንትዮቹ ገና ሳይወለዱ፣ ወይም በጎም ሆነ ክፉ ሳያደርጉ፣ የእግዚአብሔር ሐሳብ በምርጫ ይጸና ዘንድ፣ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው በመሆኑ፣ “ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” ተብሎ ተነገራት። ይህም፣ “ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዐመፃ አለን? ፈጽሞ! ለሙሴ፣ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ” ይላልና።
ሮሜ 9:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንዱ ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ፥ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ በጎ ወይም ክፉ ምንም ሳያደርጉ፥ ከጠሪው እንጂ ከሥራ ሳይሆን በምርጫ የሚሆን የእግዚአብሔር አሳብ ይጸና ዘንድ፥ ለእርስዋ፦ ታላቁ ለታናሹ ይገዛል ተባለላት። ያዕቆብን ወደድሁ ኤሳውን ግን ጠላሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም። ለሙሴ፦ የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና።
ሮሜ 9:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህም ብቻ ሳይሆን ርብቃ የነገድ አባታችን ከሆነው ከይስሐቅ መንታ ልጆችን በፀነሰች ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ምርጫ በሥራ ሳይሆን በጥሪ መሆኑን ለመግለጥ ሁለቱ ልጆች ከመወለዳቸውና ክፉም ሆነ ደግ ከማድረጋቸው በፊት እግዚአብሔር ርብቃን “ታላቁ ለታናሹ ተገዢ ይሆናል” አላት። ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለትስ ከቶ አንችልም! እግዚአብሔር ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፥ ልራራለት የምፈልገውንም እራራለታለሁ” ብሎታል።
ሮሜ 9:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ርብቃ ደግሞ ከአንድ ሰው ከአባታችን ከይስሐቅ በፀነሰች ጊዜ፥ ልጆቹ ገና ሳይወለዱ፥ መልካም ወይም ክፉ ሳያደርጉ፥ የእግዚአብሔር የምርጫው ዓላማ እንዲጸና፥ በሥራ ሳይሆን ከጠሪው ስለሆነ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል፤” ተብሎ ተነግሮአት ነበር። “ያዕቆብን ወደድሁ፥ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው። እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላልን? በጭራሽ! ሙሴን “የምምረውን እምረዋለሁ፥ ለምራራለትም እራራለታለሁ” ብሎታልና።