ሮሜ 2:5-13
ሮሜ 2:5-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ልቡናህን እንደ ማጽናትህ፥ ንስሓም እንደ አለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔር እውነተና ፍርድ በሚገለጥበት ቀን መቅሠፍትን ለራስህ ታከማቻለህ። እርሱ በእውነተና ፍርዱ ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋልና። በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ፥ ምስጋናና ክብርን፥ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ለሚክዱና እውነትን ለሚለውጡ፥ ዐመፅንም ለሚወድዱ ሰዎች ዋጋቸው ቍጣና መቅሠፍት ነው። መከራና ጭንቀት አስቀድሞ በአይሁዳዊ፥ ደግሞም በአረማዊ፥ ሥራዉ ክፉ በሆነ ሰው ሁሉ ላይ ነው። ምስጋናና ክብር፥ ሰላምም አስቀድሞ ለአይሁዳዊ፥ ደግሞም ለአረማዊ፥ ሥራዉ መልካም ለሆነ ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና። ከሕግ ወጥተው የበደሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ያለ ሕግ የበደሉ ሁሉም ያለ ሕግ ይፈረድባቸዋል። በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና።
ሮሜ 2:5-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን በራስህ ላይ ቍጣን ታከማቻለህ። እግዚአብሔር “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል”። በጎ የሆነውን ጸንቶ በማድረግ ክብርን፣ ሞገስንና ዘላለማዊነትን ለሚሹ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራስ ወዳዶች፣ እውነትን ትተው ክፋትን በሚከተሉ ፍርድና ቍጣ ይደርስባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ በማንኛውም ሰው፣ አስቀድሞ በአይሁድ ከዚያም በአሕዛብ ላይ መከራና ጭንቀት ይሆናል፤ ነገር ግን በጎ ለሚሠራ ለማንኛውም፣ አስቀድሞ ለአይሁድ ከዚያም ለአሕዛብ ክብር፣ ሞገስና ሰላም ይሆንለታል፤ እግዚአብሔር ለማንም አያደላምና። ሕግ ሳይኖራቸው ኀጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኀጢአት የሠሩ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን የሚባሉት ለሕጉ የሚታዘዙ እንጂ፣ ሕጉን የሚሰሙ አይደሉም።
ሮሜ 2:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል። ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና። ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።
ሮሜ 2:5-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ አንተ ንስሓ ባለመግባትህና እልኸኛ በመሆንህ የእግዚአብሔር ቊጣና ትክክለኛ ፍርድ በሚገለጥበት ቀን ቅጣትህ እንዲበዛ ታደርጋለህ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ እንደየሥራው ይሰጠዋል። በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናና ክብርን የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚፈልጉ እግዚአብሔር የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል። የራሳቸውን ጥቅም በሚፈልጉ፥ ለእውነት በማይታዘዙና ለዐመፅ በሚታዘዙ ዐድመኞች ላይ ግን የእግዚአብሔር ቊጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። በመጀመሪያ በአይሁድ፥ ቀጥሎም በአሕዛብ ክፋት በሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ላይ መከራና ጭንቀት ይመጣባቸዋል። ነገር ግን መልካም ነገርን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ለአይሁድም ሆነ ለአሕዛብ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር በሰዎች መካከል አያዳላም። ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ ሕጉ ባይኖራቸውም ይጠፋሉ፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ ግን በሕጉ ይፈረድባቸዋል። በእግዚአብሔር ፊት የሚጸድቁ ሕጉን ሰምተው በሥራ ላይ የሚያውሉት ናቸው እንጂ ሕጉን ሰምተው በሥራ ላይ የማያውሉት አይደሉም።
ሮሜ 2:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ ሰው ሁሉ ላይ፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፤ ነገር ግን መልካምን ለሚሠራ ሁሉ አስቀድሞ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ምስጋና፥ ክብርና ሰላም ይሆንለታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ማዳላት የለምና። ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚፈፅሙት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙት አይጸድቁምና።