ወደ ሮሜ ሰዎች 2:5-13

ወደ ሮሜ ሰዎች 2:5-13 መቅካእኤ

ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሓ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን በራስህ ላይ ቁጣን ታከማቻለህ። እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤ በመልካም ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘለዓለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ በራስ ወዳዶች፥ ለእውነት በማይታዘዙት ነገር ግን ለዐመፃ በሚታዘዙት ላይ ቁጣና መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። ክፉ በሚያደርግ ሰው ሁሉ ላይ፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ከዚያም በግሪካዊ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፤ ነገር ግን መልካምን ለሚሠራ ሁሉ አስቀድሞ አይሁዳዊ ከዚያም ግሪካዊ ምስጋና፥ ክብርና ሰላም ይሆንለታል። በእግዚአብሔር ዘንድ ማዳላት የለምና። ሕግ ሳይኖራቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግ እያላቸው ኃጢአት የሠሩ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚፈፅሙት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙት አይጸድቁምና።