መዝሙር 88:3-8
መዝሙር 88:3-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ፥ ዘርህን ለዘለዓለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ አጸናለሁ። አቤቱ፥ ሰማያት ክብርህን ጽድቅህንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ። እግዚአብሔርን በደመናት ማን ይተካከለዋል? ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል? እግዚአብሔር በቅዱሳን ምክር ክቡር ነው፤ በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው። አቤቱ የኀያላን አምላክ፥ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? አቤቱ፥ አንተ ብርቱ ነህ፥ እውነትም ይከብብሃል።
መዝሙር 88:3-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነፍሴ በመከራ ተሞልታለችና፤ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ተቃርባለች። ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱት ጋራ ተቈጠርሁ፤ ዐቅምም ዐጣሁ። በሙታን መካከል እንደ ተጣሉ፣ ተገድለው በመቃብር ውስጥ እንደ ተጋደሙ፣ አንተ ከእንግዲህ እንደማታስባቸው፣ ከእጅህም ወጥተው እንደ ተወገዱ ሆንሁ። በዐዘቅት ጥልቀት ውስጥ ጣልኸኝ፤ በጨለማ ጕድጓድ ውስጥ ከተትኸኝ። የቍጣህ ክብደት በላዬ ዐርፏል፤ በማዕበልህም ሁሉ አጥለቅልቀኸኛል። ሴላ የሚቀርቡኝ ባልንጀሮቼን ከእኔ አራቅህ፤ እንዲጸየፉኝም አደረግህ፤ ተከብቤአለሁ፤ ማምለጥም አልችልም፤
መዝሙር 88:3-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ መከራ ስለ ደረሰብኝ ለመሞት ተቃርቤአለሁ። ሞተው ወደ መቃብር ከሚወርዱት ሰዎች ጋር ተቈጥሬአለሁ፤ ምንም ረዳት እንደሌለው ሰው ሆኜአለሁ። በሙታን መካከል ፈጽሞ እንደ ተተዉ፥ ተገድለው በመቃብር እንደ ተጋደሙ፥ ከእንግዲህ ፈጽሞ እንደማታስታውሳቸውና የአንተ እንክብካቤ ከእነርሱ እንደ ተቋረጠ ሰዎች መስዬአለሁ። አንተ ወደ መቃብር አዘቅት ወደ ጨለመውና ጥልቅ ወደ ሆነው ጒድጓድ አወረድከኝ። ቊጣህ እጅግ ከብዶኛል፤ የቊጣህም ማዕበል አጥለቅልቆኛል። ወዳጆቼ ሁሉ ከእኔ እንዲርቁ አደረግህ፤ በፊታቸውም አጸያፊ አደረግኸኝ፤ ዙሪያዬ ታጥሮአል፤ ማምለጫም የለኝም።
መዝሙር 88:3-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፥ ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና። ወደ ጉድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ለዘለዓለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፥ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ። በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጉድጓድ አስቀመጥኸኝ። በእኔ ላይ ቁጣህ ጸና፥ ማዕበልህንም ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ።