መዝሙር 78:1-20
መዝሙር 78:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕዝቤ ሆይ፤ ትምህርቴን ስማ፤ ጆሮህንም ወደ አንደበቴ ቃል አዘንብል። አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከጥንት በነበረ እንቈቅልሽ እናገራለሁ፤ ይህም የሰማነውና ያወቅነው፣ አባቶቻችንም የነገሩን ነው። እኛም ከልጆቻቸው አንደብቀውም፤ የእግዚአብሔርን ምስጋና፣ ኀይሉንና ያደረገውን ድንቅ ሥራ፣ ለሚቀጥለው ትውልድ እንናገራለን። ለያዕቆብ ሥርዐትን መሠረተ፤ በእስራኤልም ሕግን ደነገገ፤ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ፣ አባቶቻችንን አዘዘ። ይህም የሚቀጥለው ትውልድ እንዲያውቅ፣ እነርሱም በተራቸው ለልጆቻቸው፣ ገና ለሚወለዱትም እንዲነግሩ ነው። እነርሱም በእግዚአብሔር ይታመናሉ፤ የእርሱንም ሥራ አይረሱም፤ ትእዛዞቹንም ይጠብቃሉ። ነገር ግን እንደ አባቶቻቸው፣ እልኸኞችና ዐመፀኞች፣ ልቡን ያላቀና፣ መንፈሱም በእግዚአብሔር የማይታመን ትውልድ አይሆኑም። የኤፍሬም ልጆች የታጠቁ ቀስተኞች ቢሆኑም፣ በጦርነት ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ። የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፤ በሕጉም መሠረት ለመሄድ እንቢ አሉ። እርሱ የሠራውን ሥራ፣ ያሳያቸውንም ድንቅ ነገር ረሱ። አባቶቻቸው በዐይናቸው እያዩ፣ በግብጽ አገር፣ በጣኔዎስ ምድር ታምራት አደረገ። ባሕሩን ከፍሎ አሻገራቸው፤ ውሃውንም እንደ ክምር አቆመ። ቀን በደመና መራቸው፤ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን። ዐለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ እንደ ባሕር የበዛ ውሃ አጠጣቸው፤ ምንጭ ከቋጥኝ አፈለቀ፤ ውሃን እንደ ወንዝ አወረደ። እነርሱ ግን በምድረ በዳ በልዑል ላይ በማመፅ፣ በርሱ ላይ ኀጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ። እጅግ የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ፣ እግዚአብሔርን በልባቸው ተፈታተኑት። እንዲህም ብለው በእግዚአብሔር ላይ ተናገሩ፤ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማእድ ማሰናዳት ይችላልን? ዐለቱን ሲመታ፣ ውሃ ተንዶለዶለ፤ ጅረቶችም ጐረፉ፤ ታዲያ፣ እንጀራንም መስጠት ይችላል? ሥጋንስ ለሕዝቡ ሊያቀርብ ይችላል?”
መዝሙር 78:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕዝቤ ሆይ! ትምህርቴን አድምጥ፤ ቃሌንም በጥንቃቄ ስማ፤ ንግግሬን በምሳሌ እጀምራለሁ፤ ከጥንት ጀምሮ የተሰወረውን ምሥጢር እገልጣለሁ። ስለ ሰማናቸውና ስለ ዐወቅናቸው፥ አባቶቻችንም ስለ ነገሩን ነገሮች እናገራለሁ፤ እነዚህን ነገሮች ከልጆቻችን አንሰውርም፤ ስለ እግዚአብሔር ኀይል፥ ስላከናወናቸውም ታላላቅ ሥራዎችና ስላደረጋቸው ድንቅ ነገሮች ለተከታዩ ትውልድ እንናገራለን። እርሱ ሥርዓትን ለያዕቆብ ልጆች ዐወጀ፤ ለእስራኤልም ሕግን መሠረተ፤ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ የቀድሞ አባቶቻችንን አዘዛቸው። ይህንንም ያደረገው ተከታዩ ትውልድ እንዲያውቀውና ለልጆቹም እንዲያስተምረው ነው። በዚህ ዐይነት እነርሱም በእግዚአብሔር ላይ ይታመናሉ፤ ትእዛዞቹንም ዘወትር ይፈጽማሉ እንጂ ያደረገውን ሁሉ አይረሱም። እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና እምቢተኞች አይሆኑም፤ እነዚያ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ አልነበሩም፤ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልኖሩም። የኤፍሬም ልጆች ቀስትና ፍላጻ ይዘው ሳለ በጦርነት ቀን ሸሹ። ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን አልጠበቁም፤ ሕጉንም ለመፈጸም እምቢ አሉ። ያሳያቸውን ተአምራት ሁሉ እና ያደረገውን መልካም ነገር ሁሉ ረሱ። በግብጽ አገር በጾዓን ሜዳ የቀድሞ አባቶቻቸው እያዩ እግዚአብሔር በፊታቸው ተአምራትን አደረገ። ባሕሩን ከፍሎ በመካከሉ አሳለፋቸው፤ ውሃው እንደ ግንብ እንዲቆም አደረገ። ቀን በደመና፥ ሌሊት በእሳት ብርሃን መራቸው። በበረሓ አለቱን ሰነጠቀ፤ ከዚያም ከጥልቅ ባሕር የሚገኘውን ያኽል ብዙ ውሃ ሰጣቸው። ምንጭን ከአለት አፈለቀ፤ ውሃውም እንደ ወንዝ እንዲፈስስ አደረገ። እነርሱ ግን እግዚአብሔርን በመበደል ኃጢአት መሥራት ቀጠሉ፤ በበረሓም በልዑል እግዚአብሔር ላይ ዐመፁ። የተመኙትን ምግብ በመጠየቅ ሆን ብለው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት። እንዲህ እያሉም በእግዚአብሔር ላይ አጒረመረሙ፤ “እግዚአብሔር በበረሓ ማእድ ዘርግቶ ምግብ ሊሰጥ ይችላልን? አለቱን መሰንጠቁና ውሃም እንደ ጐርፍ ማፍሰሱ እውነት ነው፤ ታዲያ፥ ምግብን ሊሰጠን፥ ሥጋንም ሊያዘጋጅልን ይችላል ማለት ነውን?”
መዝሙር 78:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፥ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ። አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፥ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም እንቆቅልሽ እናገራለሁ። የሰማነውንና ያወቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ከልጆቻቸው አንሰውረውም፥ ለሚመጣውም ትውልድ የጌታን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት እንናገራለን። ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፥ የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው እንዲናገሩ ነው፥ ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፥ እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ዐመፀኛና የሚያስመርር ትውልድ፥ ልቡን ያላቀና ትውልድ፥ መንፈሱም በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነ። የኤፍሬም ልጆች ለውጊያ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በጦርነት ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ። የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፥ መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥ በግብጽ አገርና በጾዓን አገር በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት። ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፥ ውኆችን እንደ ግንብ አቆመ። ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን። ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፥ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው። ውኃን ከዓለት አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ። ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት። የተመኙትን መብል እየጠየቁ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት። እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት፦ “እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን? ዓለቱን መታ፥ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፥ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?”