መዝሙር 15:1-5
መዝሙር 15:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ በአንተ ታምኛለሁና ጠብቀኝ። እግዚአብሔርን አልሁት፥ “አንተ ጌታዬ ነህ፤ በጎነቴን አትሻትምና። ፈቃድህ ሁሉ በምድር ባሉት ቅዱሳን ላይ ተገለጠ። ደዌያቸው በዛ፤ ከዚያም በኋላ ተፋጠኑ፤ በደም ማኅበራቸው አልተባበርም። ስማቸውንም በአፌ አልጠራም። እግዚአብሔር የርስቴ ዕድል ፋንታና ጽዋዬ ነው፥ ርስቴን የምትመልስ አንተ ነህ።
መዝሙር 15:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ኰረብታህስ ማን መኖር ይችላል? አካሄዱ የቀና፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር፤ በምላሱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉ የማይሠራ፤ ወዳጁን የማያማ፤ ነውረኛ በፊቱ የተናቀ፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ግን የሚያከብር፤ ዋጋ የሚያስከፍለውም ቢሆን፣ ቃለ መሐላውን የሚጠብቅ፤ ገንዘቡን በዐራጣ የማያበድር፣ በንጹሓን ላይ ጕቦ የማይቀበል።
መዝሙር 15:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ወደ መኖሪያህ መግባት የሚችል ማን ነው? በተቀደሰችው ተራራህስ ላይ ሊኖር የሚችል ማን ነው? እርሱ ነቀፋ የሌለበት ሕይወትን የሚኖርና ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ፥ ከልቡም እውነትን የሚናገር፥ ሌሎች ሰዎችን የማያማ፥ በጓደኞቹ ላይ ክፉ ነገር የማያደርግ፥ በጐረቤቱ ላይ አሉባልታን የማያሠራጭ፥ ክፉ ሰዎችን የሚንቅ፥ ለእግዚአብሔር የሚታዘዙትን ግን የሚያከብር፥ ምንም ያኽል ከባድ ቢሆን የገባውን ቃል ኪዳን የሚፈጽም፥ ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ ንጹሕ ሰዎችን ለመጒዳት ጉቦ የማይቀበል፥ እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ከቶ አይናወጥም። በሰላም ይኖራል እንጂ ከቶ አይናወጥም።
መዝሙር 15:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውም ተራራህ ማን ይኖራል? በቅንነት የሚሄድ፥ ጽድቅንም የሚያደርግ፥ በልቡም እውነትን የሚናገር። በአንደበቱ የማይሸነግል፥ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፥ የሚቀርቡትን የማይሰድብ። ኃጢአተኛ ሰው በፊቱ የተናቀ፥ ጌታን የሚፈሩትን የሚያከብር፥ ቢጎዳም የማለውን የማይከዳ። ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፥ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘለዓለም አይታወክም።