መዝሙር 139:5-10
መዝሙር 139:5-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገዴም ዕንቅፋትን አኖሩ። እግዚአብሔርንም፥ “አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ” አልሁት። አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የድኅነቴ ኀይል፥ በጦርነት ቀን በራሴ ላይ ሁነህ ሰወርኸኝ። አቤቱ፥ ጌታዬ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኀጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፥ እንዳይታበዩም አትተወኝ። የአሽክላቸው ራስ የከንፈራቸውም ክፋት ይድፈናቸው። የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ መቆም እንዳይችሉ በችግር ወደ ምድር ይውደቁ።
መዝሙር 139:5-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንተ ከኋላም ከፊትም ዙሪያዬን ከለልኸኝ፤ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እንዲህ ያለው ዕውቀት ለእኔ ድንቅ ነው፤ ልደርስበትም የማልችል ከፍ ያለ ነው። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፣ አንተ በዚያ አለህ፤ መኝታዬንም በሲኦል ባደርግ በዚያ ትገኛለህ። በንጋት ክንፍ ተነሥቼ ብበርር፣ እስከ ባሕሩ ዳርቻ መጨረሻ ብሄድ፣ በዚያም ቢሆን እጅህ ትመራኛለች፤ ቀኝ እጅህም አጥብቃ ትይዘኛለች።
መዝሙር 139:5-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዙሪያዬ ሁሉ ትገኛለህ፤ በኀይልህም ትጠብቀኛለህ። የአንተ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ ነው፤ እኔ ላስተውለው ከምችለው በላይ ነው። ከአንተ ለማምለጥ ወዴት መሄድ እችላለሁ? ከፊትህስ ርቄ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ እዚያ ትገኛለህ፤ ወደ ሙታን ዓለም ብወርድ በዚያም አንተ አለህ። ከፀሐይ መውጫ ባሻገር በርሬ ብሄድ፥ ወይም በፀሐይ መግቢያ በኩል ርቄ ብኖር፥ እዚያ ተገኝተህ በእጅህ ትመራኛለህ፤ በቀኝ እጅህም ትደግፈኛለህ።