መዝሙር 107:35-43
መዝሙር 107:35-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣ ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ። የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤ ብዙ ፍሬም አመረቱ። ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም። በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤ በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤ መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው። ድኾችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤ ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ። ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤ ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች። እንግዲህ ማንም ብልኅ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።
መዝሙር 107:35-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንደገናም በበረሓው ብዙ ኲሬዎች እንዲኖሩ፥ በደረቁም ምድር ብዙ ምንጮች እንዲገኙ አደረገ። የተራቡ ሕዝቦች በዚያ እንዲሰፍሩ አደረገ፤ እነርሱም የሚኖሩባቸውን ከተሞች ሠሩ። በእርሻዎች ላይ እህልን ዘሩ፤ ወይንን ተከሉ፤ ብዙ መከርም ሰበሰቡ። ሕዝቡን ባረካቸው፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ፤ የከብቶቻቸውም ቊጥር እንዳያንስ አደረገ። በጭቈና፥ በችግርና በሐዘን ተሸንፈው በተዋረዱ ጊዜ ግን፥ እግዚአብሔር ልዑላኑን አዋረደ፤ በምድረ በዳም አሸዋ ውስጥ እንዲንከራተቱ አደረገ። ችግረኞችንም ከሥቃያቸው አወጣቸው፤ እንደ በግ መንጋ የበዙ ልጆችንም ሰጣቸው። ቅኖች ይህን በማየት ደስ ይላቸዋል፤ ክፉዎች ግን ዐፍረው ዝም ይላሉ። ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ ይህን ያስተውሉ፤ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን የፍቅር ሥራ ይገንዘቡ።
መዝሙር 107:35-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ምድረ በዳን ወደ ውኃ ማጠራቀምያ፥ ደረቁንም ምድር ወደ ውኃ ምንጭነት ቀየረ። በዚያም ረሀብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። እርሻዎችንም ዘሩ፥ ወይኖችንም ተከሉ፥ ፍሬንም ሰበሰቡ። ባረካቸውም እጅግም በዙ፥ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም። እነርሱ በጭቈና፥ በስቃይና በኃዘን ተዋርደው እያነሱ ሄዱ፥ በመኰንኖችም ላይ ውርደትን ዘረገፈ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አንከራተታቸው። ችግረኛንም ከመከራው አወጣው፥ ቤተሰቦችን እንደ በጎች መንጋ አበዛ። ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፥ ክፋት በሙሉ አፉን ይዘጋል። ጠቢብ ማነው? ይህንን ይፈጽም፥ እርሱ የጌታንም ጽኑ ፍቅር ይገነዘባል።