መዝሙር 107:35-43

መዝሙር 107:35-43 NASV

ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣ ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ። የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤ የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ። በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤ ብዙ ፍሬም አመረቱ። ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤ የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም። በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣ ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤ በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤ መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው። ድኾችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤ ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ። ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤ ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች። እንግዲህ ማንም ብልኅ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።