ምሳሌ 7:10-23
ምሳሌ 7:10-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የምንዝር ጌጥ ያላት የጐልማሶችን ልብ እንዲሰቀል የምታደርግ ሴት ያንጊዜ ትገናኘዋለች። እርስዋ የምትበርር መዳራትንም የምትወድ ናት። ሁከተኛና አበያ ናት፥ እግሮችዋም በቤቷ አያርፉም፥ አንድ ጊዜ በጎዳና፥ በሌላ ጊዜም በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች። ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊቷም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው፦ “የፍቅሬ መሥዋዕት ነው፤ ዛሬ ስእለቴን እሰጣለሁ። ስለዚህ እንድገናኝህ መጣሁ፥ ፊትህንም ለማየት ስሻ አገኘሁህ። በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብፅንም ሸመልመሌ ምንጣፍ። በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ። ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ። በመልካም መተቃቀፍም ደስ ይበለን። ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤ በእጁም የወርቅ ከረጢት ይዞአል፤ ወደ ቤቱ ቢመለስም ከብዙ ጊዜ በኋላ ነው።” በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ወጥመድም ትጐትተዋለች። እርሱ አንገቱን ደፍቶ ይከተላታል፥ ለመታረድ እንደሚነዳ በሬ፥ ወደ እስራት እንደሚሄድ ውሻ፥ ሆዱ እንደ ተወጋ ዋሊያ፥ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል ዎፍ፥ ሳያውቅም ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሮጥ።
ምሳሌ 7:10-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም አንዲት ሴት ልታገኘው ወጣች፤ እንደ ዝሙት ዐዳሪ ለብሳ፣ ለማሳሳት ታጥቃ። ጯኺና ማን አለብኝ ባይ ናት፤ እግሮቿ ዐርፈው ቤት አይቀመጡም፤ አንዴ በመንገድ፣ አንዴ በአደባባይ፣ በየማእዘኑም ታደባለች። አፈፍ አድርጋ ይዛ ሳመችው፤ ኀፍረቷንም ጥላ እንዲህ አለችው፤ “በቤቴ የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ፤ ስለዚህ አንተን ለማግኘት ወጣሁ፤ ፈልጌህ ነበር፤ ይኸው አገኘሁህ። ዐልጋዬን ከግብጽ የመጣ፣ ጌጠኛ በፍታ አልብሼዋለሁ። ዐልጋዬን፣ የከርቤ፣ የአደስና የቀረፋ ሽቱ አርከፍክፌበታለሁ። ና፤ እስኪነጋ በጥልቅ ፍቅር እንርካ፤ በፍቅር ራሳችንን እናስደስት። ባሌ እቤት የለም፤ ሩቅ አገር ሄዷል። በገንዘብ የተሞላ ቦርሳ ወስዷል፤ ጨረቃዋ ሙሉ እስክትሆን አይመለስም።” በሚያግባቡ ቃላት አሳተችው፤ በለሰለሰ አንደበቷ አታለለችው። ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ፣ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ አጋዘን፣ ሳያንገራግር ተከተላት፤ ፍላጻ ጕበቱን እስኪወጋው ድረስ፣ ሕይወቱን እንደሚያሳጣው ሳያውቅ፣ በርራ ወደ ወጥመድ እንደምትገባ ወፍ ሆነ።
ምሳሌ 7:10-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚያም በኋላ ሴትዮዋ ወጣችና አገኘችው፤ አለባበስዋም ሴትኛ ዐዳሪ መሆኗን ያመለክት ነበር፤ ሰውንም የምታስትበት ዕቅድ ነበራት። እርስዋ ደፋርና ኀፍረተቢስ ሴት ነበረች፤ በቤትዋ መቀመጥ ስለማያስደስታት ዘወትር ትዞራለች፤ በየማእዘኑ፥ በየመንገዱና በየገበያ ስፍራ እየቆመች ትጠባበቃለች። ያንን ወጣት ዕቅፍ አድርጋ ሳመችው፤ ያለ ኀፍረት እንዲህ አለችው፦ “እኔ መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ የስእለቴን መባ አቅርቤአለሁ፤ ስለዚህ አንተን ለመቀበል ወጣሁ፤ በብርቱም ፈለግኹህ፤ እነሆም አገኘሁህ! ከግብጽ አገር የመጣውን ጌጠኛ አንሶላ በአልጋዬ ላይ አንጥፌአለሁ። ከርቤ አልሙንና ቀረፋ ከተባሉት ቅመሞች የተሠራ ሽቶ አርከፍክፌበታለሁ። ና ሌሊቱን ሙሉ በፍቅር እንርካ፤ በመተቃቀፍም ደስ ይበለን! ባሌ በቤት የለም፤ ወደ ሩቅ አገር ሄዶአል፤ ብዙ ገንዘብ ይዞ ስለ ሄደ እስከ ሁለት ሳምንት አይመለስም።” በሚማርኩ ቃሎችዋ አግባባችው፤ በለዘበ አነጋገርዋም አታለለችው። በሬ ወደሚታረድበት ስፍራ እንደሚነዳ፥ አጋዘንም ቸኲሎ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ፥ ወዲያውኑ እርስዋን ተከትሎ ሄደ፤ ፍላጻም ሆድ ዕቃውን እንደሚወጋው ዐይነት ሆነ፤ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ ወፍ መሰለ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ሕይወቱ በአደጋ ላይ ለመውደቅ መቃረቡን አላወቀም።
ምሳሌ 7:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የአምንዝራ ሴት ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች። ሁከተኛና እንቢተኛ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፥ አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች። ያዘችውም ሳመችውም፥ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው፦ “መሥዋዕትንና የደኅንነት ቁርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፥ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ። ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም። በአልጋዬ ላይ ማለፊያ የአልጋ ልብስ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ያማሩ አልባሳት አንጥፌበታለሁ። በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ። ና፥ እስኪ ነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን። ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፥ በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፥ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል።” በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፥ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች። እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንደሚነዳ፥ አጋዘን ቸኩሎ ወደ ወጥመድ እንደሚገባ፥ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚጣደፍ፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ።