ምሳሌ 26:17-23
ምሳሌ 26:17-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በሌሎች ጠብ ጥልቅ የሚል መንገደኛ፣ የውሻ ጆሮ እንደሚይዝ ሰው ነው። ትንታግ ወይም የሚገድል ፍላጻ እንደሚወረውር እብድ፣ “ቀልዴን እኮ ነው” እያለ ባልንጀራውን የሚያታልል ሰውም እንደዚሁ ነው። ዕንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሻኪ ከሌለም ጠብ ይበርዳል። ከሰል ፍምን፣ ዕንጨትም እሳትን እንደሚያቀጣጥል፣ አዋኪ ሰውም ጠብን ያባብሳል። የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሰው ውስጠኛው ክፍል ዘልቆ ይገባል። ክፋትን በልብ ቋጥሮ ለስላሳ ቃል የሚናገር ከንፈር፣ በብር ፈሳሽ እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው።
ምሳሌ 26:17-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በማይመለከትህ ነገር መከራከር በመንገድ የሚተላለፈውን የውሻ ጆሮ እንደ መያዝ ይቈጠራል። ሰውን አታሎ “በቀልድ ነው ያደረግኹት” የሚል ሰው በአደገኛ የጦር መሣሪያ እንደሚጫወት ዕብድ ሰው ነው። እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል፤ አሾክሿኪ ከሌለም ጠብ ይቆማል። ከሰል ፍምን፥ እንጨትም እሳትን እንደሚያበዛ ጠብ አጫሪ ሰው ጠብን ያባብሳል። የአሾክሻኪ ቃል እንደ ጣፋጭ ምግብ ደስ እያሰኘ እስከ ውስጥ ሰውነት ይወርዳል። በልቡ ክፋት እያለ በአንደበቱ ልዝብ ቃል የሚናገር ሰው ውጪው በሚያምር በብር ቀለም እንደ ተቀባ የሸክላ ዕቃ ነው።
ምሳሌ 26:17-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በማይመለከተው ገብቶ የሚሟገት፥ ውሻን በጆሮው እንደሚይዝ ነው። ትንታግንና ፍላጻን ሞትንም እንደሚወረውር እንደ ዕብድ ሰው፥ ባልንጀራውን የሚያታልል፦ “ስቀልድ ነው” የሚል ሰውም እንዲሁ ነው። እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል፥ ጆሮ ጠቢ በሌለበትም ዘንድ ጠብ ጸጥ ይላል። ከሰል ፍምን እንጨትም እሳትን እንዲያበዛ፥ እንዲሁ ቁጡ ሰው ጠብን ያበዛል። የጆሮ ጠቢ ቃል እንደ ጣፋጭ መብል ነው፥ እርሱም እስከ ሆድ ጉርጆች ድረስ ይወርዳል። ክፋት በልቡ ሳለ ፍቅርን የሚናገር ከንፈር በብር ዝገት እንደተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው።