ፊልጵስዩስ 4:10-23
ፊልጵስዩስ 4:10-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጌታችን እጅግ ደስ አለኝ፤ ቢሳናችሁ እንኳ አሁንም እንደምታስቡልኝ፥ ከዱሮ ጀምሮ ለእኔ ችግር ታስቡ፥ ትተጉም ነበርና። ይህንም የምል ስለ አጣሁ አይደለም፤ ያለኝ እንደሚበቃኝ አውቃለሁና። እኔ ችግሩንም፥ ምቾቱንም እችላለሁ፤ ራቡንም፥ ጥጋቡንም፥ ማዘኑንም፥ ደስታውንም፥ ሁሉን በሁሉ ለምጀዋለሁ፤ በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ነገር ግን በመከራዬ ጊዜ ተባባሪዎች መሆናችሁ መልካም አደረጋችሁ። እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች፤ በመጀመሪያው ትምህርት ከመቄዶንያ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን፥ በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ እናንተ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄም ሳለሁ ደግሞ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ለችግሬ ላካችሁልኝ። ይህንም የማነሣሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጂ። ነገር ግን ሁሉ አለኝ፤ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን፥ ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ አሟልቻለሁ። ፈጣሪዬ እንደ ባለጸግነቱ መጠን፥ በክብር በኢየሱስ ክርስቶስ የምትሹትን ሁሉ ይፈጽምላችኋል። ለአባታችን ለእግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ምስጋና ይሁን አሜን። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን ሁሉ ሰላም በሉ፤ በእኔ ዘንድ ያሉ ወንድሞቻችንም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳንም ሁሉ፥ ይልቁንም ከቄሣር ቤተ ሰብእ የሆኑ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በጢሞቴዎስና በአፍሮዲጡ እጅ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።
ፊልጵስዩስ 4:10-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደ አዲስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር። ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ። ሆኖም የመከራዬ ተካፋይ ስለ ሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል። ከዚህም በላይ፣ እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ወንጌልን በተቀበላችሁ ጊዜ ከመቄዶንያ ስነሣ፣ ከእናንተ በቀር በመስጠትና በመቀበል የትኛውም ቤተ ክርስቲያን አልተባበረኝም። በተሰሎንቄ በነበርሁበት ጊዜ እንኳ፣ በችግሬ ወቅት ደጋግማችሁ ርዳታ ልካችሁልኛልና። ይኸውም፣ ትርፉ ለእናንተ እየበዛ እንዲሄድ እንጂ ስጦታውን ጓጕቼ አይደለም። የሚያስፈልገኝን ሁሉ፣ ከሚያስፈልገኝም በላይ ተቀብያለሁ፤ የላካችሁትንም ስጦታ ከአፍሮዲጡ እጅ ተቀብዬ ተሞልቻለሁ፤ ይህም መዐዛው የጣፈጠ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእኔ ጋራ ያሉት ወንድሞችም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ፣ በተለይም ከቄሳር ቤተ ሰው የሆኑት ወገኖች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።
ፊልጵስዩስ 4:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
ፊልጵስዩስ 4:10-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና ለእኔ ችግር ማሰብ ስለ ጀመራችሁ በጌታ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፤ ይህንንም ስል የአሰባችሁትን በሥራ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ አላገኛችሁም ነበር ማለቴ ነው እንጂ ስለ እኔ ችግር ማሰባችሁን አቋርጣችኋል ማለቴ አይደለም። ደግሞም ይህን የምለው ለኑሮዬ የሚያስፈልገኝን በማጣቴ አይደለም፤ እኔማ “ያለኝ ነገር ይበቃኛል” ማለትን ተምሬአለሁ። ስለዚህ ማግኘትንም ሆነ ማጣትን ዐውቃለሁ፤ በማንኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የመጥገብንና የመራብን፥ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ። ይሁን እንጂ እናንተ የችግሬ ተካፋዮች ሆናችሁ በመገኘታችሁ መልካም አደረጋችሁ። ከዚህም በቀር ወንጌልን ለማብሠር በጀመርኩበት ጊዜ ከመቄዶንያ ስወጣ ከእናንተ በፊልጵስዩስ ከምትገኙት አማኞች በቀር በመስጠትም ሆነ በመቀበል ከእኔ ጋር የተባበረ ሌላ ማኅበረ ምእመናን እንዳልነበረ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄም ችግር እንደ ደረሰብኝ ዐውቃችሁ መላልሳችሁ ርዳታ ልካችሁልኛል። ይህንንም ስል የእናንተን ስጦታ ለማግኘት በመጓጓት ሳይሆን የልግሥናችሁ ፍሬ እንዲበዛላችሁ በመመኘት ነው። የሚያስፈልገኝንና ከሚያስፈልገኝም በላይ የላካችሁልኝን ስጦታ ከኤጳፍሮዲቱስ እጅ ተቀብዬአለሁ፤ ይህም የእናንተ ስጦታ በመልካም መዓዛ እንደ ተሞላ መሥዋዕት እግዚአብሔር የሚቀበለውና ደስ የሚሰኝበት ነው። ስለዚህም አምላኬ ከክብሩ ብልጽግና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሰጣችኋል። ለአባታችንና ለአምላካችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ለምእመናን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ሌሎችም አማኞች ሁሉ በተለይም ከሮማው ንጉሠ ነገሥት ቤተሰቦች የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ፊልጵስዩስ 4:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደገና ማሰብ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ተሰኝቻለሁ፤ አጋጣሚዎች አልተመቻቹላችሁም እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። ይህን ስል ስለሚያስፈልገኝ ነገር እያማረርሁ አይደለም፤ ያለኝ ነገር ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ጥቂትም ማግኘትን አውቃለሁ፤ ብዙም ማግኘትን አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ የመጥገብንና የመራብን ብዙ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ! ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተባበረ እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ ከአንድ ጊዜ በላይ የሚያስፈልገኝን ነገር ልካችሁልኝ ነበርና። ከጥሪታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታን ፈላጊ አይደለሁም። ነገር ግን የሚያስፈልገኝን ሁሉ ተቀብያለሁ፤ ተትረፍርፎልኛልም፤ መዓዛው ያማረ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከኤጳፍሮዲጡስ ተቀብዬ በሁሉ ተሟልቶልኛል። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ያሟላላችኋል። ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን።