ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደገና ለእኔ ችግር ማሰብ ስለ ጀመራችሁ በጌታ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፤ ይህንንም ስል የአሰባችሁትን በሥራ ለማሳየት መልካም አጋጣሚ አላገኛችሁም ነበር ማለቴ ነው እንጂ ስለ እኔ ችግር ማሰባችሁን አቋርጣችኋል ማለቴ አይደለም። ደግሞም ይህን የምለው ለኑሮዬ የሚያስፈልገኝን በማጣቴ አይደለም፤ እኔማ “ያለኝ ነገር ይበቃኛል” ማለትን ተምሬአለሁ። ስለዚህ ማግኘትንም ሆነ ማጣትን ዐውቃለሁ፤ በማንኛውም ቦታ ሆነ በየትኛውም ጊዜ የመጥገብንና የመራብን፥ የማግኘትንና የማጣትን ምሥጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን ነገር ማድረግ እችላለሁ። ይሁን እንጂ እናንተ የችግሬ ተካፋዮች ሆናችሁ በመገኘታችሁ መልካም አደረጋችሁ። ከዚህም በቀር ወንጌልን ለማብሠር በጀመርኩበት ጊዜ ከመቄዶንያ ስወጣ ከእናንተ በፊልጵስዩስ ከምትገኙት አማኞች በቀር በመስጠትም ሆነ በመቀበል ከእኔ ጋር የተባበረ ሌላ ማኅበረ ምእመናን እንዳልነበረ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄም ችግር እንደ ደረሰብኝ ዐውቃችሁ መላልሳችሁ ርዳታ ልካችሁልኛል። ይህንንም ስል የእናንተን ስጦታ ለማግኘት በመጓጓት ሳይሆን የልግሥናችሁ ፍሬ እንዲበዛላችሁ በመመኘት ነው። የሚያስፈልገኝንና ከሚያስፈልገኝም በላይ የላካችሁልኝን ስጦታ ከኤጳፍሮዲቱስ እጅ ተቀብዬአለሁ፤ ይህም የእናንተ ስጦታ በመልካም መዓዛ እንደ ተሞላ መሥዋዕት እግዚአብሔር የሚቀበለውና ደስ የሚሰኝበት ነው። ስለዚህም አምላኬ ከክብሩ ብልጽግና በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሰጣችኋል። ለአባታችንና ለአምላካችን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን። ለምእመናን ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ሌሎችም አማኞች ሁሉ በተለይም ከሮማው ንጉሠ ነገሥት ቤተሰቦች የሆኑት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:10-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች