ዘኍልቍ 21:1-3
ዘኍልቍ 21:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በአዜብ በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የአራድ ንጉሥ በአታሪን መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። እስራኤልም ለእግዚአብሔር፥ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ብትሰጠን እርሱንና ከተሞቹን ሕርም ብለን እናጠፋዋለን” ብለው ስእለት ተሳሉ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፤ ከነዓናውያንንም አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱንም፥ ከተሞቻቸውንም ሕርም ብለው አጠፉአቸው፤ የዚያን ስፍራ ስም “ሕርም” ብለው ጠሩት።
ዘኍልቍ 21:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በኔጌብ ይኖር የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ እስራኤል በአታሪም መንገድ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በእስራኤላውያን ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። በዚያ ጊዜ እስራኤል፣ “ይህን ሕዝብ አሳልፈህ በእጃችን ከሰጠኸን ከተሞቻቸውን ፈጽሞ እንደመስሳለን” ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልመና ሰምቶ ከነዓናውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰዎቹንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ከዚህ የተነሣም ስፍራው ሖርማ ተባለ።
ዘኍልቍ 21:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ። እስራኤልም ለእግዚአብሔር፦ እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።
ዘኍልቍ 21:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
መኖሪያው ኔጌብ የነበረ የከነዓናውያን ንጉሥ ዐራድ እስራኤላውያን በአታሪም በኩል መምጣታቸውን በሰማ ጊዜ በእነርሱ ላይ አደጋ ጥሎ ጥቂቶቹን ማረከ። በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን “ይህን ሕዝብ ድል እንድንነሣው ብትረዳን፥ እነርሱንም ሆኑ ከተሞቻቸውን ዳግመኛ እንዳያንሰራሩ አድርገን በፍጹም እንደመስሳቸዋለን” በማለት ለእግዚአብሔር ተሳሉ። እግዚአብሔርም ልመናቸውን ሰምቶ ስለ ረዳቸው ከነዓናውያንን ድል ነሥተው ያዙ፤ ስለዚህ እስራኤላውያን እነርሱንና ከተሞቻቸውን ፈጽመው ደመሰሱ፤ ፈጽሞ የተደመሰሱ መሆናቸውንም ለማመልከት ያን ስፍራ “ሖርማ” ብለው ሰየሙት።
ዘኍልቍ 21:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል መምጣቱን ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ጦርነት አደረገ ከእርሱም ምርኮ ማረከ። እስራኤልም ለጌታ እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ፦ “እነዚህን ሕዝቦች ፈጽሞ አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ።” ጌታም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።