ማርቆስ 14:27-42

ማርቆስ 14:27-42 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛዉን እመታለሁ፤ በጎችም ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ “ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም፤” አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ፤ ትጉም፤” አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና “አባ አባት ሆይ! ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን፤” አለ። መጣም፤ ተኝተውም አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም “ስምዖን ሆይ! ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አለው። ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ደግሞም መጥቶ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ሦስተኛም መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው።

ማርቆስ 14:27-42 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “ ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ’ ከተነሣሁ በኋላ ግን፣ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።” ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አልሰናከልም” አለ። ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋራ ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ከርሱ ጋራ ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዝናለች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ ቢቻል ሰዓቱ ከርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፣ “አባ፣ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፣ “ስምዖን ሆይ፤ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደ ገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየ። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደ ተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል! ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል! ተነሡ፤ እንሂድ! እነሆ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”

ማርቆስ 14:27-42 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም፦ በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው። ጴጥሮስም፦ ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው። ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ፦ ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም፦ ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና፦ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና፦ አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ። መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም፦ ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው፥ ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ሦስተኛም መጥቶ፦ እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።

ማርቆስ 14:27-42 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “ ‘እረኛውን መትቼ እገድላለሁ፤ በጎቹም ይበተናሉ፤’ ተብሎ ተጽፎአልና ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ፤ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ትታችሁኝም ትሸሻላችሁ፤ ነገር ግን ከሞት ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜአችሁ እሄዳለሁ።” በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ እንኳ ቢክዱህ፥ እኔ ከቶ አልክድህም!” አለው። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት አንተ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። ጴጥሮስ ግን “መሞት እንኳ ቢያስፈልግ ከአንተ ጋር እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም!” እያለ አጠንክሮ ተናገረ። የቀሩትም ደቀ መዛሙርት እንዲሁ ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፦ “እኔ እዚያ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም አስከትሎ ሄደ፤ እዚያም እጅግ ያዝንና ይጨነቅ ጀመረ። እንዲህም አላቸው፦ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዝናለች፤ እዚህ ቈዩ፤ ተግታችሁም ጠብቁ።” ከእነርሱ ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ፤ በመሬትም ላይ በግንባሩ ተደፍቶ የሚቻል ቢሆን ያቺ ሰዓት እንድታልፍለት ጸለየ። እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፥ ሁሉ ነገር ይቻልሃል፤ ይህን የመከራ ጽዋ ከእኔ አርቅልኝ፤ ነገር ግን እንደ አንተ ፈቃድ እንጂ እንደ እኔ ፈቃድ አይሁን።” ወደ ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ተኝተው አገኛቸው፤ ስለዚህ ጴጥሮስን፦ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት እንኳ ልትነቃ አልቻልክምን?” አለው። “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አላቸው። እንደገናም ሄዶ፥ ያንኑ የፊተኛውን ቃል በመናገር ጸለየ። ደግሞም ተመልሶ በመጣ ጊዜ፥ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ስለ ነበር፥ ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛም ጊዜ ወደ እነርሱ መጥቶ፥ እንዲህ አላቸው፦ “አሁንም ገና ተኝታችኋልን? አሁንም ዕረፍት ታደርጋላችሁን? እንግዲህስ በቃ! ሰዓቱ ደርሶአል! እነሆ! የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ ተላልፎ ይሰጣል። በሉ ተነሡ! እንሂድ! አሳልፎ የሚሰጠኝ ይኸው ቀርቦአል!”

ማርቆስ 14:27-42 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤ “እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ” ከተነሣሁ በኋላ ግን፥ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ። ጴጥሮስም፥ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ። ኢየሱስም፥ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ፥ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው። ጴጥሮስም፥ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቆዩ” አላቸው። ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። ደግሞም፥ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው። ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ፥ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፥ “አባ፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፤ “ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው።” እንደገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየው። ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር። ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።”