የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 14:27-42

የማ​ር​ቆስ ወን​ጌል 14:27-42 አማ2000

ኢየሱስም “በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ ‘እረኛዉን እመታለሁ፤ በጎችም ይበተናሉ፤’ የሚል ተጽፎአልና። ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም፤” አለው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፤” አለው። እርሱም ቃሉን አበርትቶ “ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም፤” አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ። ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፤ ደቀ መዛሙርቱንም “ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ፤” አላቸው። ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ፤ ትጉም፤” አላቸው። ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና “አባ አባት ሆይ! ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን፤” አለ። መጣም፤ ተኝተውም አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም “ስምዖን ሆይ! ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው፤” አለው። ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ። ደግሞም መጥቶ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አላወቁም። ሦስተኛም መጥቶ “እንግዲህስ ተኙ፤ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኀጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል። ተነሡ፤ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል፤” አላቸው።