ማቴዎስ 8:4-17
ማቴዎስ 8:4-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ “ጌታ ሆይ!ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል” ብሎ ለመነው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ “ጌታ ሆይ! በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፤ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም ‘ሂድ’ ብለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና’ ብለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም ‘ይህን አድርግ’ ብለው ያደርጋል” አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም ለመቶ አለቃ “ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ፤” አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋንም ዳሰሰ፤ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ “እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ መናፍስትን በቃኣሉ አወጣ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
ማቴዎስ 8:4-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ኢየሱስ፣ “መፈወስህን ለማንም አታውራ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ሙሴ ያዘዘውንም መባ አቅርብ፤ ይህም ምስክር ይሆንላቸዋል” አለው። ኢየሱስ ቅፍርናሆም እንደ ደረሰ አንድ የመቶ አለቃ ቀርቦ፣ እንዲህ ሲል ለመነው፤ “ጌታ ሆይ፤ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ በመሠቃየት ከቤት ተኝቷል” አለው። ኢየሱስም፣ “እኔ መጥቼ ልፈውሰውን?” አለው። የመቶ አለቃው ግን መልሶ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ቤቴ እንድትገባ የሚገባኝ አይደለሁም፤ ነገር ግን ከዚሁ ሆነህ አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል፤ እኔ ራሴ የምታዘዛቸው አለቆች፣ ለእኔም የሚታዘዙ የበታቾች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን፣ ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን፣ ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ ባሪያዬንም፣ ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም በመልሱ ተደንቆ ይከተሉት ለነበሩት እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእስራኤል መካከል እንኳ እንዲህ ያለ እምነት ያለው አንድ ሰው አላገኘሁም፤ እላችኋለሁ፣ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ በመንግሥተ ሰማይ ከአብርሃም፣ ከይሥሐቅና ከያዕቆብ ጋራ በማእድ ይቀመጣሉ፤ መንግሥተ ሰማይ ተዘጋጅቶላቸው የነበሩት ግን ወደ ውጭ ወደ ጨለማው ይጣላሉ። በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም መቶ አለቃውን፣ “ሂድ! እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። ብላቴናውም በዚያች ቅጽበት ተፈወሰ። ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት ጐራ ሲል የጴጥሮስ ዐማት በትኵሳት ታምማ ተኝታ አገኛት። እጇን ዳሰሳት፤ ትኵሳቱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በዚያ ምሽት በአጋንንት የተያዙ ብዙ ሰዎችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም መናፍስትን በቃሉ አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። በዚህም ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ፤ “እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ።”
ማቴዎስ 8:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም፦ ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው። ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው። ኢየሱስም፦ እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው። የመቶ አለቃውም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው። ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም ለመቶ አለቃ፦ ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ፦ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ መናፍስትን በቃኣሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
ማቴዎስ 8:4-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፥ ከለምጹ የዳነውን ሰው እንዲህ አለው፤ “ይህን ነገር ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ መዳንህን ለካህን አሳይ፤ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ፥ ስለ መዳንህ ሙሴ ያዘዘውን መባ ለእግዚአብሔር አቅርብ” አለው። ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ከተማ በገባ ጊዜ፥ አንድ ሮማዊ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ፥ አገልጋዬ ሽባ ሆኖ፥ እጅግ በመሠቃየት በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃው ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ቤቴ እንድትገባ እኔ የተገባሁ ሰው አይደለሁም፤ ነገር ግን አንዲት ቃል ብቻ ተናገር፤ አገልጋዬም ይድናል። እኔ ራሴ ለባለ ሥልጣኖች ታዛዥ ስሆን፥ ከእኔ በታች የማዛቸው ወታደሮች አሉኝ፤ ከእነርሱ አንዱን ‘ሂድ!’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውንም ‘ና!’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬም ‘ይህን አድርግ!’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ ተደነቀ፤ ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህን የሚያኽል ትልቅ እምነት ያለው አንድም ሰው በእስራኤል ስንኳ አላገኘሁም። ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅ፥ ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በማዕድ ይቀመጣሉ እላችኋለሁ። የዚህ መንግሥት ወራሾች መሆን ይገባቸው የነበሩት ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ። በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ከዚህ በኋላ፥ ኢየሱስ የመቶ አለቃውን “ሂድ፤ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” አለው። አገልጋዩም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ። ከዚያ ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ የጴጥሮስ ዐማት አተኲሶአት ታማ እንደ ተኛች አየ። እጅዋንም በዳሰሳት ጊዜ፥ ወዲያው ትኩሳቱ ለቀቃትና ዳነች፤ ተነሥታም ኢየሱስን ታገለግል ጀመር። በመሸም ጊዜ ሰዎች በአጋንንት የተያዙ ብዙ በሽተኞችን ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ እርሱም በቃሉ ርኩሳን መናፍስትን አስወጣ፤ በሽተኞችንም ሁሉ ፈወሰ። ይህንንም በማድረጉ በነቢዩ ኢሳይያስ፥ “እርሱ ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ” የተባለው ትንቢት ተፈጸመ።
ማቴዎስ 8:4-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም እንዲህ ሲል መለሰ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ከባለሥልጣኖች በታች ነኝ፤ ከእኔ በታች ደግሞ ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ደግሞ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ይከተሉት የነበሩትን እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥቱ ልጆች ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም ለመቶ አለቃው “ሂድና እንደ እምነትህ ይሁንልህ፤” አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ አማቱ በትኩሳት ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋን ዳሰሳት፤ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ መናፍስቶቹን ሁሉ በቃል አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ። ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ “እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ፤” የተባለው እንዲፈጸም ነው።