ኢየሱስም “ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ” አለው። ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ በመለመን፥ “ጌታ ሆይ! ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሠቃየ በቤት ተኝቶአል” አለው። ኢየሱስም “እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ” አለው። የመቶ አለቃውም እንዲህ ሲል መለሰ “ጌታ ሆይ! ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፤ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ራሴ ከባለሥልጣኖች በታች ነኝ፤ ከእኔ በታች ደግሞ ወታደሮች አሉኝ፤ አንዱን ‘ሂድ’ ስለው ይሄዳል፤ ሌላውን ደግሞ ‘ና’ ስለው ይመጣል፤ አገልጋዬንም ‘ይህን አድርግ’ ስለው ያደርጋል።” ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ይከተሉት የነበሩትን እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም። እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ፤ ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋርም በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤ የመንግሥቱ ልጆች ግን ውጪ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም ለመቶ አለቃው “ሂድና እንደ እምነትህ ይሁንልህ፤” አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ። ኢየሱስ ወደ ጴጥሮስ ቤት በገባ ጊዜ አማቱ በትኩሳት ታማ ተኝታ አያት፤ እጅዋን ዳሰሳት፤ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለችው። በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደሩባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ መናፍስቶቹን ሁሉ በቃል አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ። ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ “እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ፤” የተባለው እንዲፈጸም ነው።
የማቴዎስ ወንጌል 8 ያንብቡ
ያዳምጡ የማቴዎስ ወንጌል 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማቴዎስ ወንጌል 8:4-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች