ሉቃስ 3:2-6
ሉቃስ 3:2-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ወራት የእግዚአብሔር ቃል በምድረ በዳ ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ መጣ። ስለ ኀጢአት ስርየት ለንስሓ የሚያበቃ ጥምቀትን እየሰበከ በዮርዳኖስ አውራጃ ዞረ። በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምፅ በነቢዩ በኢሳይያስ መጽሐፍ ቃል እንደ ተጻፈ፥ እንዲህ ሲል፥ “የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ። ጐድጓዳው ሁሉ ይምላ፤ ተራራውም፥ ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ሰንከልካላውም የቀና ጥርጊያ ይሁን፤ ወጣ ገባው መንገድም ይስተካከል። ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትድግና ይይ።”
ሉቃስ 3:2-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። እርሱም ለኀጢአት ስርየት የሚሆን የንስሓን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ወዳሉት ስፍራዎች ሁሉ መጣ፤ ይኸውም፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በመጽሐፉ እንዲህ ሲል በጻፈው ቃል መሠረት ነበር፤ “በምድረ በዳ እንዲህ ብሎ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጐዳናውንም አቅኑ፤ ሸለቆው ሁሉ ይሞላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው መንገድ ቀና፣ ወጣ ገባውም ጐዳና ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል፤ የሰውም ዘር ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ያያል።’ ”
ሉቃስ 3:2-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል መጽሐፍ፦ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ ተብሎ እንደ ተጻፈ ለኃጢአት ስርየት የንስሐን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለችው አገር ሁሉ መጣ።
ሉቃስ 3:2-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሐናና ቀያፋም የካህናት አለቆች ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ በበረሓ ሳለ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ስለዚህ ዮሐንስ፥ በዮርዳኖስ ወንዝ ዙሪያ ባሉት አገሮች ሁሉ እየተዘዋወረ፦ “ለኃጢአታችሁ ይቅርታ እንድታገኙ ንስሓ ገብታችሁ ተጠመቁ፤” እያለ ያስተምር ነበር። ይህም የሆነው፦ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ዮሐንስ አስቀድሞ እንዲህ ሲል በጻፈው መሠረት ነው፦ “እነሆ! ይህ በበረሓ እንዲህ እያለ የሚጮኽ ሰው ድምፅ ነው፤ ‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ! ጥርጊያውንም አቅኑ! ጐድጓዳው ቦታ ሁሉ ይደልደል! ተራራና ኰረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል! ጠማማው መንገድ ይቅና! ሻካራውም መንገድ ይስተካከል! ሰውም ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ!’ ”
ሉቃስ 3:2-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት በነበሩበት ዘመን፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። በዮርዳኖስም ዙርያ ወዳለው አገር ሁሉ መጥቶ ለኃጢአት ስርየት የንስሓን ጥምቀት ሰበከ፤ የነቢዩ ኢሳይያስ ቃላት በሚገኘበት መጽሐፍ እንደተጻፈው፦ “በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፤ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ ጐድጓዳው ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፤ ጠማማውም መንገድ ቀና ይሁን፤ ሸካራውም መንገድ የተስተካከለ ይሁን፤ ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤”