ኢያሱ 9:3-6
ኢያሱ 9:3-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በገባዖን የሚኖሩ ሰዎች ግን እግዚአብሔር በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አድርገው መጡ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፤ በትከሻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ ረዋት ተሸከሙ። በእግራቸውም ያደረጉት ጫማ ያረጀና ማዘቢያው የተበጣጠሰ፥ ልብሳቸውም በላያቸው ያረጀ ነበረ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀ፥ የሻገተና የተበላሸ ነበረ። ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ጉባኤ ወደ ጌልገላ መጥተው ለኢያሱና ለእስራኤል ሁሉ፥ “ከሩቅ ሀገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ” አሉ።
ኢያሱ 9:3-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ላይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፣ ለማታለል ፈለጉ፤ ስለዚህም ያረጀ ስልቻና የተጣፈ አሮጌ የወይን ጠጅ አቍማዳ በአህያ የጫነ መልእክተኛ መስለው ሄዱ። ሰዎቹም ያረጀና የተጠጋገነ ነጠላ ጫማ አድርገዋል፤ አሮጌ ልብስ ለብሰዋል፤ ለስንቅ የያዙት እንጀራም በሙሉ የደረቀና የሻገተ ነበር። ከዚያም ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ኢያሱንና የእስራኤልን ሰዎች፣ “የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን ግቡ” አሏቸው።
ኢያሱ 9:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፥ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ። ያረጀ የተጠቀመም ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፥ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች፦ ከሩቅ አገር መጥተናል፥ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን አድርጉ አሉ።
ኢያሱ 9:3-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በዐይ ከተማዎች ላይ ያደረገውን ሁሉ ስለ ሰሙ፤ እርሱን ለማታለል ወሰኑ፤ እነርሱም ስንቃቸውን አዘጋጅተው፥ አሮጌ ስልቻና ቀዳዳው ተለጥፎ የተሰፋ የወይን ጠጅ አቁማዳ በአህዮች ጫኑ፤ ተቀዳዶ ያለቀ አሮጌ ልብስ ለብሰው፥ የተጠጋገነ እላቂ ጫማ አደረጉ፤ ለስንቅ የያዙትም እንጀራ ደረቅና የሻገተ ነበር። ይህን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በጌልገላ ወደሚገኘው ሰፈር ሄደው ኢያሱንና እስራኤላውያንን፦ “እኛ የመጣነው ከሩቅ አገር ነው፤ የመጣነውም ከእናንተ ጋር የቃል ኪዳን ውል ለማድረግ ነው” አሉአቸው።
ኢያሱ 9:3-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠገነም የወይን ጠጅ አቁማዳ ጫኑ። ያረጀና የተጠጋገነ ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች እንዲህ አሉ፦ “ከሩቅ አገር መጥተናል፤ እንግዲህ አሁን ከእኛ ጋር የቃል ኪዳን አድርጉ።”