ኢያሱ 6:8-21

ኢያሱ 6:8-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ይሄዱ ዘንድ ኢያሱ እንደ ነገ​ራ​ቸው ሰባቱ ካህ​ናት የተ​ቀ​ደሱ ሰባ​ቱን ቀንደ መለ​ከት ይዘው ሄዱ፤ በሄ​ዱም ጊዜ አሰ​ም​ተው በም​ል​ክት ነፉ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የሕጉ ታቦት ትከ​ተ​ላ​ቸው ነበር። ሰል​ፈ​ኞ​ችም ፊት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህ​ና​ቱም ነጋ​ሪት ይመቱ ነበር፤ ከታ​ቦቱ በኋላ ይከ​ተሉ የነ​በ​ሩ​ትም ቀንደ መለ​ከ​ቱን እየ​ነፉ ይሄዱ ነበር። ኢያ​ሱም ሕዝ​ቡን፦ እን​ዳ​ይ​ጮኹ ማንም ድም​ፃ​ቸ​ውን እን​ዳ​ይ​ሰማ፥ እን​ዲ​ጮኹ እስ​ኪ​ያ​ዛ​ቸ​ውም ድረስ ከአ​ፋ​ቸው ቃል እን​ዳ​ይ​ወጣ አዘ​ዛ​ቸው። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደች፤ ከተ​ማ​ዪ​ቱ​ንም ዞረች፤ ወደ ሰፈ​ርም ተመ​ልሳ በዚያ አደ​ረች። ኢያ​ሱም በማ​ግ​ሥቱ ማለዳ ተነሣ፤ ካህ​ና​ቱም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሕ​ጉን ታቦት ተሸ​ከሙ። ሰባ​ቱም ካህ​ናት ሰባ​ቱን ቀንደ መለ​ከት ይዘው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለ​ከ​ቱ​ንም ይነፉ ነበር፤ ተዋ​ጊ​ዎ​ችም በፊ​ታ​ቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀ​ሩ​ትም ሕዝብ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የቃል ኪዳን ታቦት በኋላ ይሄዱ ነበር፤ ካህ​ና​ቱም ቀንደ መለ​ከ​ቱን ይነፉ ነበር። በሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም ቀን የቀ​ረው ሕዝብ ሁሉ ከተ​ማ​ዪ​ቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመ​ለሱ፤ ስድ​ስት ቀንም እን​ዲህ አደ​ረጉ። በሰ​ባ​ተ​ኛ​ውም ቀን በነጋ ጊዜ ማል​ደው ተነሡ፤ እን​ደ​ዚ​ህም ከተ​ማ​ዪ​ቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚ​ያም ቀን ብቻ ከተ​ማ​ዪ​ቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። እን​ዲ​ህም ሆነ፤ ከተ​ማ​ዪ​ቱን ሰባት ጊዜ በዞ​ሩና ካህ​ናቱ ቀንደ መለ​ከ​ቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእ​ስ​ራ​ኤል ልጆች አለ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከተ​ማ​ዪ​ቱን ሰጥ​ቶ​አ​ች​ኋ​ልና ጩኹ። ከተ​ማ​ዪ​ቱም በእ​ር​ስ​ዋም ያለው ሁሉ ለሠ​ራ​ዊት ጌታ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እርም ይሆ​ናሉ፤ የላ​ክ​ና​ቸ​ውን መል​እ​ክ​ተ​ኞች ስለ ሸሸ​ገች ዘማ​ዊቱ ረዓብ፥ ከእ​ር​ስ​ዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕ​ይ​ወት ይኖ​ራሉ። እና​ንተ ግን እርም ብለን ከተ​ው​ነው እን​ዳ​ት​ወ​ስዱ ተጠ​ን​ቀቁ፤ ከእ​ር​ሱም ተመ​ኝ​ታ​ችሁ አት​ው​ሰዱ፤ ብት​ወ​ስዱ ግን የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ሰፈር የተ​ረ​ገ​መች ታደ​ር​ጓ​ታ​ላ​ችሁ፤ እኛ​ንም ታጠ​ፉ​ና​ላ​ችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የና​ስና የብ​ረ​ትም ዕቃ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​ቀ​ደሰ ይሁን፤ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝ​ቡም ጮኹ፥ ካህ​ና​ቱም ቀንደ መለ​ከ​ቱን ነፉ፤ ሕዝ​ቡም የቀ​ንደ መለ​ከ​ቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥ​ሩም ወደቀ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ ወደ ከተ​ማ​ዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታ​ቸው ወደ ከተ​ማ​ዪቱ ሮጡ፤ ከተ​ማ​ዪ​ቱ​ንም እጅ አደ​ረጉ። ኢያ​ሱም ከተ​ማ​ዋን፥ በከ​ተ​ማ​ዪ​ቱም ውስጥ የነ​በ​ሩ​ትን ሁሉ፥ ከወ​ንድ እስከ ሴት፥ ከሕ​ፃን እስከ ሽማ​ግሌ፥ ከበሬ እስከ በግና እስከ አህያ በሰ​ይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋ።

ኢያሱ 6:8-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢያሱም ለሕዝቡ ከተናገረ በኋላ፣ ሰባቱ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው መለከታቸውን እየነፉ ወደ ፊት ቀደሙ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦትም ተከተላቸው። የታጠቁ ተዋጊዎችም መለከት ከሚነፉት ካህናት ፊት ቀድመው ሲሄዱ፣ ደጀን የሆኑት ጠባቂዎች ደግሞ ታቦቱን ተከተሉ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ መለከቶቹ ባለማቋረጥ ይነፉ ነበር። ኢያሱ ሕዝቡን፣ “የማሸበሪያ ጩኸት አታሰሙ፤ ድምፃችሁ ከፍ ብሎ አይሰማ፤ ጩኹ እስከምላችሁም ቀን ድረስ ከአፋችሁ አንዲት ቃል አትውጣ፤ የምትጮኹት ከዚያ በኋላ ነው” ሲል አዘዛቸው። ስለዚህ ኢያሱ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው፣ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ እንዲዞሩ አደረገ። ከዚያም ሕዝቡ ወደ ሰፈር ተመልሰው ዐደሩ። ኢያሱ በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እየሄዱ፣ መለከቱን ባለማቋረጥ ይነፉ ጀመር፤ የታጠቁ ተዋጊዎችም እነዚህን በመቅደም ሲሄዱ፣ የደጀን ጠባቂዎቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ታቦት ይከተሉ ነበር፤ ካህናቱም ሳያቋርጡ መለከት ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ከዞሩ በኋላ ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀን ሙሉም እንዲሁ አደረጉ። በሰባተኛው ቀን ገና ጎሕ ሲቀድ ተነሡ፤ እንደ በፊቱም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ የዞሯትም በዚያ ቀን ብቻ ነው። በሰባተኛው ዙር ላይ ካህናቱ መለከቱን ሲነፉ፣ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሰጥቷችኋልና ጩኹ ከተማዪቱና በውስጧ ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ስለ ሆነ ፈጽማችሁ አጥፉ እኛ የላክናቸውን ሰላዮች ስለ ሸሸገች ጋለሞታዪቱ ረዓብ ብቻና ከርሷ ጋራ በቤቷ ውስጥ ያሉት ሁሉ ይትረፉ። እናንተ ግን ዕርም ከሆኑት ነገሮች አንዳች በመውሰድ በራሳችሁ ላይ ጥፋት እንዳታመጡ እጃችሁን ሰብስቡ፤ አለዚያ የእስራኤልን ሰፈር ለጥፋት ትዳርጋላችሁ፤ ክፉ ነገር እንዲደርስበትም ታደርጋላችሁ፤ ብሩና ወርቁ እንዲሁም የናሱና የብረቱ ዕቃ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስለ ሆነ፣ ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት ይግባ።” መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱም ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች። በከተማዪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፣ ማለትም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን፣ ከብቱንና በጉን እንዲሁም አህያውን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።

ኢያሱ 6:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ሰልፈኞቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የቀረውም ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታንሡ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፥ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ ብሎ አዘዛቸው። እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፥ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ። ኢያሱም ማለዳ ተነሣ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፥ ሰልፈኞቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፥ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፥ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፥ እንደዚህም ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፥ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን አለ፦ እግዚአብሔር ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፥ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱ ረዓብ ከእርስዋም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፥ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደ ሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁትማላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፥ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ። ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፥ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።

ኢያሱ 6:8-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢያሱ ሕዝቡን ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀንደ መለከት የያዙ ሰባት ካህናት ቀንደ መለከቱን እየነፉ ወደፊት ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ተከተላቸው። ወታደሮቹም ቀንደ እምቢልታ ከሚነፉት ካህናት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱ እምቢልታውን ሳያቋርጡ እየነፉ ሕዝቡ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። ኢያሱ ግን፦ “ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ እንዳትጮኹ፤ ወይም ድምፃችሁ እንዳይሰማ፤ እንዲያውም አንዲት ቃል እንኳ እንዳትናገሩ፤ ጩኹ ስላችሁ በዚያን ጊዜ ትጮኻላችሁ” ብሎ ሕዝቡን አዘዘ። በዚህ ዐይነት የእግዚአብሔር ታቦት ከተማዋን አንድ ጊዜ እንዲዞር አደረገ፤ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ፥ ወደ ሰፈሩ ተመልሶ በዚያ ዐዳር ሆነ። በማግስቱ ኢያሱ በማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱን እምቢልታ የያዙት ሰባት ካህናት እምቢልታቸውን ሳያቋርጡ እየነፉ ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት ለፊት ሄዱ፤ መለከቱ ሳያቋርጥ እየተነፋ ወታደሮቹ ከካህናቱ ቀድመው ሌላው ሕዝብ ደግሞ ከታቦቱ በኋላ ይከተል ነበር። በዚህም በሁለተኛው ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ እስከ ስድስት ቀንም በዚሁ ዐይነት አደረጉ። በሰባተኛው ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሥተው በዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩአት፤ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩበት ቀን ይህ ብቻ ነበር። በሰባተኛው ዙር ካህናቱ እምቢልታ ሊነፉ በሚዘጋጁበት ጊዜ ኢያሱ ሕዝቡን፦ “እግዚአብሔር ከተማይቱን ስለ ሰጣችሁ ጩኹ!” ብሎ አዘዘ። “በከተማይቱና በውስጡ ያለው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር የተረገመ ሆኖ መደምሰስ አለበት፤ ሴትኛ ዐዳሪዋ ግን የላክናቸውን ሰላዮች ደብቃ ስላዳነች መትረፍ የሚገባቸው እርስዋና ከእርስዋ ጋር በቤትዋ ያሉት ብቻ ናቸው። እናንተ ግን በእስራኤል ሰፈር ችግርንና ጥፋትን እንዳታስከትሉ መደምሰስ ከሚገባቸው ነገሮች ማናቸውንም ጓጒታችሁ ከመውሰድ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ብርና ወርቅ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር የተለየ ይሁን፤ እርሱም በእግዚአብሔር የዕቃ ግምጃ ቤት መቀመጥ አለበት።” ስለዚህ እምቢልታ ተነፋ፤ ሕዝቡም የእምቢልታውን ድምፅ በሰማ ጊዜ ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ አሰሙ የከተማይቱም ቅጽሮች ፈረሱ፤ ከዚህም በኋላ ሠራዊቱ ኮረብታውን ወጥቶ ሰተት ብሎ ወደ ከተማይቱ በመግባት በቊጥጥሩ ሥር አደረጋት፤ ሰይፋቸውንም መዘው በከተማይቱ የተገኘውን ወንዱንም ሴቱንም ወጣቱንና ሽማግሌውን ሁሉ ገደሉ፤ የከብት፥ የበግና የአህያውን መንጋ ሁሉ ፈጁ።

ኢያሱ 6:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢያሱም ለሕዝቡ በተናገረ ጊዜ፥ ሰባቱ ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ፊት ሄዱ ቀንደ መለከቱንም ነፉ፤ የጌታ ቃል ኪዳን ታቦት ይከተላቸው ነበር። ተዋጊዎቹም ቀንደ መለከቱን በሚነፉ በካህናቱ ፊት ይሄዱ ነበር፥ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከታቦቱ በኋላ ይሄድ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “እኔ፦ ጩኹ እስከምልበት ቀን ድረስ አትጩኹ፥ ድምፃችሁንም አታሰሙ፥ ከአፋችሁም አንድ ቃል አይውጣ፤ ከዚያን በኋላ ግን ትጮኻላችሁ።” እንዲሁ የጌታን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማይቱን አዞረው፤ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው በዚያ አደሩ። ከዚያም በኋላ ኢያሱ ማልዶ ተነሣ፤ ካህናቱም የጌታን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ይዘው በጌታ ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎቹም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የኋላ ደጀንም የሆነው ሕዝብ ከጌታ ታቦት በኋላ ይመጡ ነበር፥ ካህናቱም እየሄዱ ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን ከተማይቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን ጎሕ ሲቀድ ማልደው ተነሡ፥ ተመሳሳይ በሆነ ሥርዓት ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያ ቀን ብቻ ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። በሰባተኛውም ጊዜ ካህናቱ ቀንደ መለከቱን ሲነፉ ኢያሱ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ጌታ ከተማይቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማይቱም በእርሷም ያለው ሁሉ ለጌታ እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልክተኞች ስለ ሸሸገች አመንዝራይቱ ረዓብ ከእርሷም ጋር በቤትዋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ካደረጋችሁት በኋላ እርም ከሆነው ነገር ራሳችሁን ጠብቁ፤ እርም ከሆነው አንዳች የወሰዳችሁ እንደሆነ የእስራኤልን ሰፈር የተረገመ ታደርጉታላችሁ፥ ታስጨንቁታላችሁም። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ የናስና የብረትም ዕቃ ለጌታ የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ ጌታም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ በቀጥታ አቅንቶ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ያዝዋት። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ።