በእግዚአብሔርም ፊት ይሄዱ ዘንድ ኢያሱ እንደ ነገራቸው ሰባቱ ካህናት የተቀደሱ ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው ሄዱ፤ በሄዱም ጊዜ አሰምተው በምልክት ነፉ፤ የእግዚአብሔርም የሕጉ ታቦት ትከተላቸው ነበር። ሰልፈኞችም ፊት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ነጋሪት ይመቱ ነበር፤ ከታቦቱ በኋላ ይከተሉ የነበሩትም ቀንደ መለከቱን እየነፉ ይሄዱ ነበር። ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንዳይጮኹ ማንም ድምፃቸውን እንዳይሰማ፥ እንዲጮኹ እስኪያዛቸውም ድረስ ከአፋቸው ቃል እንዳይወጣ አዘዛቸው። የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደች፤ ከተማዪቱንም ዞረች፤ ወደ ሰፈርም ተመልሳ በዚያ አደረች። ኢያሱም በማግሥቱ ማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የሕጉን ታቦት ተሸከሙ። ሰባቱም ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎችም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በኋላ ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። በሁለተኛውም ቀን የቀረው ሕዝብ ሁሉ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ። በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፤ እንደዚህም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያም ቀን ብቻ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። እንዲህም ሆነ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ በዞሩና ካህናቱ ቀንደ መለከቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች አለ፥ “እግዚአብሔር ከተማዪቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። ከተማዪቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱ ረዓብ፥ ከእርስዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። እናንተ ግን እርም ብለን ከተውነው እንዳትወስዱ ተጠንቀቁ፤ ከእርሱም ተመኝታችሁ አትውሰዱ፤ ብትወስዱ ግን የእስራኤልን ሰፈር የተረገመች ታደርጓታላችሁ፤ እኛንም ታጠፉናላችሁ። ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።” ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታቸው ወደ ከተማዪቱ ሮጡ፤ ከተማዪቱንም እጅ አደረጉ። ኢያሱም ከተማዋን፥ በከተማዪቱም ውስጥ የነበሩትን ሁሉ፥ ከወንድ እስከ ሴት፥ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፥ ከበሬ እስከ በግና እስከ አህያ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋ።
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 6:8-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች