ዮሐንስ 13:1-35

ዮሐንስ 13:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከፋ​ሲካ በዓል አስ​ቀ​ድሞ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ከዚህ ዓለም ወደ ላከው ወደ አብ ይሄድ ዘንድ ጊዜው እንደ ደረሰ ባወቀ ጊዜ በዓ​ለም ያሉ​ትን የወ​ደ​ዳ​ቸ​ውን ወገ​ኖ​ቹን ፈጽሞ ወደ​ዳ​ቸው። ራት ሲበ​ሉም አሳ​ልፎ ይሰ​ጠው ዘንድ በስ​ም​ዖን ልጅ በአ​ስ​ቆ​ሮቱ ሰው በይ​ሁዳ ልብ ሰይ​ጣን አደረ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው፥ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ወጣ፥ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እን​ደ​ሚ​ሄድ ባወቀ ጊዜ፥ ራት ከሚ​በ​ሉ​በት ተነ​ሥቶ ልብ​ሱን አኖ​ረና ማበሻ ጨርቅ አን​ሥቶ ወገ​ቡን ታጠቀ። በኵ​ስ​ኵ​ስ​ቱም ውኃ ቀድቶ የደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን እግር ያጥብ ጀመር፤ በዚያ በታ​ጠ​ቀው ማበሻ ጨር​ቅም አበሰ። ወደ ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም ደረሰ፤ እር​ሱም፥ “አቤቱ፥ አንተ እግ​ሬን ታጥ​በ​ኛ​ለ​ህን?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እኔ የም​ሠ​ራ​ውን አንተ ዛሬ አታ​ው​ቅም፤ ኋላ ግን ታስ​ተ​ው​ለ​ዋ​ለህ” ብሎ መለ​ሰ​ለት። ጴጥ​ሮ​ስም፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግ​ሬን አታ​ጥ​በ​ኝም” አለው፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እው​ነት እው​ነት እል​ሃ​ለሁ፤ እኔ እግ​ር​ህን ካላ​ጠ​ብ​ሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለ​ህም” ብሎ መለ​ሰ​ለት። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም፥ “አቤቱ፥ እን​ኪ​ያስ የም​ታ​ጥ​በኝ እጆ​ች​ንና ራሴ​ንም እንጂ እግ​ሮ​ችን ብቻ አይ​ደ​ለም፤” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “ፈጽሞ የታ​ጠበ ከእ​ግሩ በቀር ሊታ​ጠብ አያ​ስ​ፈ​ል​ገ​ውም፤ ሁለ​ን​ተ​ናው ንጹሕ ነውና፤ እና​ን​ተማ ንጹ​ሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላ​ችሁ አይ​ደ​ላ​ች​ሁም” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም አሳ​ልፎ የሚ​ሰ​ጠ​ውን ያውቅ ነበ​ርና ስለ​ዚህ “ሁላ​ችሁ ንጹ​ሓን አይ​ደ​ላ​ች​ሁም” አለ። እግ​ራ​ቸ​ው​ንም ካጠ​ባ​ቸው በኋላ ልብ​ሱን አን​ሥቶ ለበ​ሰና እንደ ገና ከእ​ነ​ርሱ ጋር ተቀ​መጠ፤ እን​ዲ​ህም አላ​ቸው፥ “ያደ​ረ​ግ​ሁ​ላ​ች​ሁን ዐወ​ቃ​ች​ሁን? እና​ንተ ‘መም​ህ​ራ​ችን፥ ጌታ​ች​ንም’ ትሉ​ኛ​ላ​ችሁ፤ መል​ካም ትላ​ላ​ችሁ፤ እኔ እን​ዲሁ ነኝና። እን​ግ​ዲህ እኔ መም​ህ​ራ​ች​ሁና ጌታ​ችሁ ስሆን እግ​ራ​ች​ሁን ካጠ​ብ​ኋ​ችሁ እና​ን​ተም እን​ዲሁ የባ​ል​ጀ​ሮ​ቻ​ች​ሁን እግር ልታ​ጥቡ ይገ​ባ​ች​ኋል። እኔ እንደ አደ​ረ​ግ​ሁ​ላ​ችሁ እና​ን​ተም ልታ​ደ​ርጉ ምሳሌ ሰጥ​ቻ​ች​ኋ​ለ​ሁና። እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ከጌ​ታው የሚ​በ​ልጥ አገ​ል​ጋይ የለም፤ ከላ​ከው የሚ​በ​ልጥ መል​እ​ክ​ተ​ኛም የለም። ይህ​ንም ዐው​ቃ​ችሁ ብት​ሠሩ ብፁ​ዓን ናችሁ። ነገር ግን ይህን የም​ና​ገር ስለ ሁላ​ችሁ አይ​ደ​ለም፤ የመ​ረ​ጥ​ኋ​ቸው እነ​ማን እንደ ሆኑ እኔ አው​ቃ​ለሁ፤ ነገር ግን መጽ​ሐፍ ‘እን​ጀ​ራ​ዬን የሚ​መ​ገብ ተረ​ከ​ዙን በእኔ ላይ አነሣ’ ያለው ይፈ​ጸም ዘንድ ነው። በሆ​ነም ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ ከመ​ሆኑ አስ​ቀ​ድሞ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ። እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ እኔ የም​ል​ከ​ውን የሚ​ቀ​በል እኔን ይቀ​በ​ላል፤ እኔ​ንም የሚ​ቀ​በል የላ​ከ​ኝን ይቀ​በ​ላል።” ይህ​ንም ተና​ግሮ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ በልቡ አዘነ፤ መሰ​ከረ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “እው​ነት እው​ነት እላ​ች​ኋ​ለሁ፤ ከእ​ና​ንተ አንዱ አሳ​ልፎ ይሰ​ጠ​ኛል።” ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ይህን ስለ ማን እንደ ተና​ገረ ተጠ​ራ​ጥ​ረው እርስ በር​ሳ​ቸው ተያዩ፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም ይወ​ደው የነ​በረ ከደቀ መዛ​ሙ​ርቱ አንዱ በጌ​ታ​ችን ኢየ​ሱስ አጠ​ገብ ተቀ​ምጦ ነበር። ስም​ዖን ጴጥ​ሮ​ስም እር​ሱን ጠቀ​ሰና፥ “ይህን ስለ ማን እንደ ተና​ገረ ጠይ​ቀህ ንገ​ረን” አለው። ያም ደቀ መዝ​ሙር በጌ​ታ​ችን ኢየ​ሱስ አጠ​ገብ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታ ሆይ፥ እርሱ ማነው?” አለው። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም መልሶ፥ “ይህ እኔ እን​ጀራ በወጥ አጥ​ቅሼ የም​ሰ​ጠው ነው” አለው፤ ያን ጊዜም እን​ጀራ በወጥ አጥ​ቅሶ ለስ​ም​ዖን ልጅ ለአ​ስ​ቆ​ሮ​ታ​ዊው ይሁዳ ሰጠው። እን​ጀ​ራ​ው​ንም ከተ​ቀ​በለ በኋላ ወዲ​ያ​ውኑ በይ​ሁዳ ልብ ሰይ​ጣን አደ​ረ​በት፤ ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስም፥ “እን​ግ​ዲህ የም​ታ​ደ​ር​ገ​ውን ፈጥ​ነህ አድ​ርግ” አለው። አብ​ረ​ው​ትም በማ​ዕድ የተ​ቀ​መ​ጡት ስለ ምን ይህን እን​ዳ​ለው አላ​ወ​ቁም። ሙዳየ ምጽ​ዋቱ በይ​ሁዳ ዘንድ ነበ​ረና፥ ለበ​ዓል የም​ን​ሻ​ውን ወይም ለነ​ዳ​ያን የም​ን​ሰ​ጠ​ውን ግዛ ያለው የመ​ሰ​ላ​ቸው ነበሩ። ይሁ​ዳም ያን እን​ጀራ ተቀ​ብሎ ወዲ​ያ​ውኑ ወጣ፥ ሌሊ​ትም ነበር።። ይሁ​ዳም ከወጣ በኋላ ያን​ጊዜ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእ​ርሱ ከበረ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ርሱ ከከ​በረ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም እር​ሱን ያከ​ብ​ረ​ዋል፥ ያን​ጊ​ዜም ያከ​ብ​ረ​ዋል። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእ​ና​ንተ ጋር አለሁ፤ ትሹ​ኛ​ላ​ችሁ፤ ለአ​ይ​ሁ​ድም እኔ ወደ​ም​ሄ​ድ​በት እና​ንተ መም​ጣት አይ​ቻ​ላ​ች​ሁም እን​ዳ​ል​ኋ​ቸው፥ አሁ​ንም ለእ​ና​ንተ እነ​ግ​ራ​ች​ኋ​ለሁ። “እርስ በር​ሳ​ችሁ ቷደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእ​ዛዝ እሰ​ጣ​ች​ኋ​ለሁ፤ እኔ እንደ ወደ​ድ​ኋ​ችሁ እና​ን​ተም እን​ዲሁ እርስ በር​ሳ​ችሁ ተዋ​ደዱ። እርስ በር​ሳ​ች​ሁም ብቷ​ደዱ፥ የእኔ ደቀ መዛ​ሙ​ርት እንደ ሆና​ችሁ በዚህ ሁሉ ያው​ቋ​ች​ኋል።”

ዮሐንስ 13:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጊዜው ልክ ከፋሲካ በዓል በፊት ነበረ፤ ኢየሱስም ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ጊዜ እንደ ደረሰ ዐወቀ። በዓለም የነበሩትን፣ የራሱ የሆኑትን ወደዳቸው፤ በፍጹም ፍቅሩም ወደዳቸው። እራትም ቀርቦ ሳለ፣ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ የስምዖንን ልጅ የአስቆሮቱን ይሁዳ ልብ አነሣሥቶ ነበር። ኢየሱስም፣ አብ ሁሉን ነገር በሥልጣኑ ሥር እንዳደረገለት፣ ከእግዚአብሔር እንደ ተላከና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚመለስ ዐውቆ፣ ከእራት ተነሣ፤ መጐናጸፊያውን አስቀመጠ፤ ወገቡንም በፎጣ ታጠቀ። ከዚያም በመታጠቢያው ውሃ ጨምሮ የደቀ መዛሙርቱን እግር እያጠበ በታጠቀው ፎጣ ያብስ ጀመር። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እግሬን ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፣ “የማደርገውን አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም፣ “የለም፤ እግሬን ከቶ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፣ “ካላጠብሁህማ ከእኔ ጋራ ዕድል ፈንታ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም ራሴንም ዕጠበኝ” አለው። ኢየሱስም፣ “ገላውን የታጠበ ሰው የሚያስፈልገው እግሩን ብቻ መታጠብ ነው፤ የቀረው አካሉ ግን ንጹሕ ነው። ሁላችሁም ባትሆኑ፣ እናንተ ንጹሓን ናችሁ” አለው። “ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ዐጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ባሪያ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ። “ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን የሚበላ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። “ሲፈጸም እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ። እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።” ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል መሰከረ። ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወድደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ፣ “ማንን ማለቱ እንደ ሆነ ጠይቀው” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “ይህን ቍራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቍራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው። ይሁዳም ቍራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ። ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው። ይሁዳም ያን ቍራሽ እንጀራ እንደ ተቀበለ ወጥቶ ሄደ፤ ሌሊትም ነበረ። ይሁዳ ከወጣ በኋላ፣ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ በርሱም እግዚአብሔር ከበረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በርሱ ከከበረ፣ እግዚአብሔር ልጁን በራሱ ዘንድ ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። “ልጆቼ ሆይ፤ ከእናንተ ጋራ የምቈየው ለጥቂት ጊዜ ነው፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ፣ ‘እኔ ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኋቸው፣ አሁንም ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ። “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”

ዮሐንስ 13:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካገባ በኋላ፥ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔር እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ፥ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም፦ “የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም” አለው። ኢየሱስም፦ “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም፦ “ጌታ ሆይ፥ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው። ኢየሱስም፦ “የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጽሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፥ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ፦ “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁ አልናገርም፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ፦ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ማናቸውንም የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ታወከ መስክሮም፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ደቀ መዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ አመንትተው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቅሶ፦ “ሰለማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። እርሱም በኢየሱስ ደረት እንዲህ ተጠግቶ፦ “ጌታ ሆይ፥ ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም፦ “እኔ ቍራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቍራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። ቍራሽም ከተቀበለ በኋላ ያን ጊዜ ሰይጣን ገባበት። እንግዲህ ኢየሱስ፦ “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ” አለው። ነገር ግን ከተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው ማንም አላወቀም፤ ይሁዳ ከረጢቱን የያዘ ስለ ሆነ፥ ኢየሱስ፦ ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፥ ወይም ለድሆች ምጽዋት እንዲሰጥ ያለው ለአንዳንዱ መስሎአቸው ነበርና። እርሱም ቍራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ። ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ እግዚአብሔርም ሰለ እርሱ ከበረ፤ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል ወዲያውም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳም፦ ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ።’ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”

ዮሐንስ 13:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እነሆ፥ ጊዜው ከአይሁድ ፋሲካ በዓል በፊት ነበር፤ ኢየሱስ ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን ዐወቀ። በዚህ በዓለም ያሉትን የራሱን ወገኖች ወዶአቸው ነበር፤ እስከ መጨረሻም ወደዳቸው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ራት ይበሉ ነበር፤ የስምዖን ልጅ አስቆሮታዊው ይሁዳ ግን ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ዲያብሎስ በልቡ ክፉ ሐሳብ አሳደረበት። አብ ሥልጣንን ሁሉ እንደ ሰጠውና ከእግዚአብሔር ወጥቶ እንደመጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ስለዚህ ከማእድ ተነሣና ልብሱን አስቀመጠ፤ ማበሻ ጨርቅም አንሥቶ በወገቡ ታጠቀ። ከዚህ በኋላ በመታጠቢያ ዕቃ ውሃ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠብ ጀመረ፤ በታጠቀውም ማበሻ ጨርቅ እግራቸውን አበሰ። ኢየሱስ ወደ ስምዖን ጴጥሮስ በመጣ ጊዜ ስምዖን ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “አንተ የእኔን እግር ከቶ አታጥብም!” አለው። ኢየሱስም “እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ድርሻ የለህም” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንዲህስ ከሆነ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንም፥ ራሴንም እጠበኝ!” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ ሁለመናውም ንጹሕ በመሆኑ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ እናንተም ንጹሖች ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” አለው። ኢየሱስ “ሁላችሁም ንጹሖች አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደ ሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው። እግራቸውን ካጠበ በኋላ ልብሱን ለበሰና ወደ ቦታው ተመልሶ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ምን እንዳደረግሁላችሁ አስተዋላችሁን? እናንተ ‘መምህርና ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ እኔ መምህርና ጌታ ስለ ሆንኩ ያላችሁት ትክክል ነው። እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን መተጣጠብ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁት እናንተም እንድታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላኪው አይበልጥም። ይህን ነገር ብታውቁና በሥራ ላይ ብታውሉት የተባረካችሁ ናችሁ። ይህን የምናገረው ስለ ሁላችሁም አይደለም፤ እኔ የመረጥኳችሁን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ‘እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ በጠላትነት ተነሣብኝ’ የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ ቃል መፈጸም አለበት። ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፤ ከተፈጸመ በኋላ፥ በእኔ ማንነት እንድታምኑ ነው። እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በመንፈሱ ተጨነቀና “እውነት፥ እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል ገልጦ ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ባለማወቃቸው እርስ በእርሳቸው ተያዩ። ኢየሱስ ይወደው የነበረው፥ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በኢየሱስ ጐን ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስ እርሱን ጠቀሰና “ስለ ማን እንደ ተናገረ እስቲ ጠይቅ” አለው። ስለዚህ እርሱ አንገቱን ወደ ኢየሱስ አስጠጋና “ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም “እርሱ ይህን እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የማጐርሰው ነው” አለ። ይህንንም ብሎ እንጀራ በወጥ አጠቀሰና የአስቆሮታዊው ስምዖን ልጅ ለሆነው ለይሁዳ አጐረሰው። ይሁዳ ጉርሻውን ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ ሰይጣን ዐደረበት፤ ኢየሱስም ይሁዳን፥ “ለማድረግ ያሰብከውን ቶሎ ብለህ አድርግ!” አለው። ኢየሱስ ስለምን ይህን እንዳለ በማእድ ከተቀመጡት ማንም የገባው የለም። ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ ወይም ለድኾች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበር። ይሁዳም ጉርሻውን እንደ ተቀበለ ወዲያውኑ ወጥቶ ሄደ፤ ጊዜውም ሌሊት ነበረ። ይሁዳ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሮአል፤ በእርሱም አማካይነት እግዚአብሔር ከብሮአል፤ እግዚአብሔር በእርሱ አማካይነት ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፤ ሳይዘገይም ያከብረዋል። ልጆቼ ሆይ፥ ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ አልቆይም፤ እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድ ባለሥልጣኖች ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው፥ አሁንም ለእናንተ እንዲሁ እላችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በእርሳችሁ ከተዋደዳችሁ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል።”

ዮሐንስ 13:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን፥ የወደዳቸውን እስከ መጨረሻው ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ፥ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው አሳብ ካስገባ በኋላ፥ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደሰጠው፥ ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣና ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ አውቆ፥ ከማእድ ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ፤ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውሃ ጨመረ፤ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ማጠብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ማበስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ! አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፤ በኋላ ግን ታስተውላለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር በጭራሽ አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ፥ ከእኔ ድርሻ የለህም፤” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! እንግዲያውስ እግሬን ብቻ ሳይሆን፥ እጄንና ራሴንም ጭምር” አለው። ኢየሱስም “ሰውነቱን የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም፤” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና “ሁላችሁ ንጹሐን አይደላችሁም” አለው። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፦ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ ስለሆንኩም መልካም ትናገራላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተም እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው አይበልጥም፤ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም፤ ይህንን ስታውቁና ስታደርጉ ብፁዓን ናችሁ። ስለ ሁላችሁም አይደለም የምናገረው፤ እኔ የመረጥኋቸውን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣብኝ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። አሁን አስቀድሜ የምነግራችሁ፥ በተከሠተ ጊዜ እኔ መሆኔን ታምኑ ዘንድ ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን ማንኛውንም ሰው የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ኢየሱስ ይህን ብሎ በመንፈሱ ተረበሸ፤ እንዲህም ሲል መሰከረ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አለ። ደቀመዛሙርቱ ስለ ማን እንደ ተናገረ ግራ ገብቶአቸው እርስ በርሳቸው ተያዩ። ከደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ይወደው የነበረው አንዱ በኢየሱስ ደረት ላይ ተጠጋ፤ ስምዖን ጴጥሮስም በምልክት “ሰለ ማን እንደ ተናገረ ንገረን” አለው። እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ! ማን ነው?” አለው። ኢየሱስም “እኔ የእንጀራ ቁራሽ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” ብሎ መለሰለት። ቁራሽም አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ለስምዖን ልጅ ለይሁዳ ሰጠው። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ሰይጣን ገባበት። ኢየሱስም “የምታደርገውን ቶሎ ብለህ አድርግ፤” አለው። ነገር ግን ስለምን ይህን እንዳለው በማእድ ከተቀመጡት ማንም አላወቀም፤ ይሁዳ የገንዘብ ከረጢቱን ይዞ ስለ ነበር፥ አንዳንዶቹ ኢየሱስ “ለበዓሉ የሚያስፈልገንን ግዛ፤ ወይም ለድሆች ምጽዋት ስጥ” ያለው መስሎአቸው ነበርና። እርሱም ቁራሹን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው ወጣ፤ ሌሊትም ነበረ። ከወጣም በኋላ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አሁን የሰው ልጅ ከብሯል፤ በእርሱም እግዚአብሔር ከብሯል፤ እግዚአብሔር ስለ እርሱ የከበረ ከሆነ፥ እግዚአብሔር ደግሞ እርሱን ራሱን ያከብረዋል፤ ወዲያውም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ! ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፤ ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁድም ‘እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም፤’ እንዳልኋቸው፥ አሁን ለእናንተ ደግሞ እላችኋለሁ። አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እርሱም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ብትዋድዱ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”