ከፋሲካ በዓል አስቀድሞ ጌታችን ኢየሱስ ከዚህ ዓለም ወደ ላከው ወደ አብ ይሄድ ዘንድ ጊዜው እንደ ደረሰ ባወቀ ጊዜ በዓለም ያሉትን የወደዳቸውን ወገኖቹን ፈጽሞ ወደዳቸው። ራት ሲበሉም አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ ሰው በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረ። ጌታችን ኢየሱስም፥ አብ ሁሉን በእጁ እንደ ሰጠው፥ ከእግዚአብሔር እንደ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም እንደሚሄድ ባወቀ ጊዜ፥ ራት ከሚበሉበት ተነሥቶ ልብሱን አኖረና ማበሻ ጨርቅ አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ። በኵስኵስቱም ውኃ ቀድቶ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ጀመር፤ በዚያ በታጠቀው ማበሻ ጨርቅም አበሰ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም ደረሰ፤ እርሱም፥ “አቤቱ፥ አንተ እግሬን ታጥበኛለህን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፤ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም፥ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆችንና ራሴንም እንጂ እግሮችን ብቻ አይደለም፤” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። ጌታችን ኢየሱስም አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ስለዚህ “ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም” አለ። እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ለበሰና እንደ ገና ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፥ “ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? እናንተ ‘መምህራችን፥ ጌታችንም’ ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከጌታው የሚበልጥ አገልጋይ የለም፤ ከላከው የሚበልጥ መልእክተኛም የለም። ይህንም ዐውቃችሁ ብትሠሩ ብፁዓን ናችሁ። ነገር ግን ይህን የምናገር ስለ ሁላችሁ አይደለም፤ የመረጥኋቸው እነማን እንደ ሆኑ እኔ አውቃለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ‘እንጀራዬን የሚመገብ ተረከዙን በእኔ ላይ አነሣ’ ያለው ይፈጸም ዘንድ ነው። በሆነም ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ ከመሆኑ አስቀድሞ እነግራችኋለሁ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የምልከውን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።” ይህንም ተናግሮ ጌታችን ኢየሱስ በልቡ አዘነ፤ መሰከረ፤ እንዲህም አለ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል።” ደቀ መዛሙርቱም ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ተጠራጥረው እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ ጌታችን ኢየሱስም ይወደው የነበረ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ስምዖን ጴጥሮስም እርሱን ጠቀሰና፥ “ይህን ስለ ማን እንደ ተናገረ ጠይቀህ ንገረን” አለው። ያም ደቀ መዝሙር በጌታችን ኢየሱስ አጠገብ ቀረብ ብሎ፥ “ጌታ ሆይ፥ እርሱ ማነው?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ይህ እኔ እንጀራ በወጥ አጥቅሼ የምሰጠው ነው” አለው፤ ያን ጊዜም እንጀራ በወጥ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮታዊው ይሁዳ ሰጠው። እንጀራውንም ከተቀበለ በኋላ ወዲያውኑ በይሁዳ ልብ ሰይጣን አደረበት፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እንግዲህ የምታደርገውን ፈጥነህ አድርግ” አለው። አብረውትም በማዕድ የተቀመጡት ስለ ምን ይህን እንዳለው አላወቁም። ሙዳየ ምጽዋቱ በይሁዳ ዘንድ ነበረና፥ ለበዓል የምንሻውን ወይም ለነዳያን የምንሰጠውን ግዛ ያለው የመሰላቸው ነበሩ። ይሁዳም ያን እንጀራ ተቀብሎ ወዲያውኑ ወጣ፥ ሌሊትም ነበር።። ይሁዳም ከወጣ በኋላ ያንጊዜ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ከበረ። እግዚአብሔር በእርሱ ከከበረ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል፥ ያንጊዜም ያከብረዋል። ልጆች ሆይ፥ ገና ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር አለሁ፤ ትሹኛላችሁ፤ ለአይሁድም እኔ ወደምሄድበት እናንተ መምጣት አይቻላችሁም እንዳልኋቸው፥ አሁንም ለእናንተ እነግራችኋለሁ። “እርስ በርሳችሁ ቷደዱ ዘንድ፥ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁም ብቷደዱ፥ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ሁሉ ያውቋችኋል።”
የዮሐንስ ወንጌል 13 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 13:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች