ኢሳይያስ 36:4-21
ኢሳይያስ 36:4-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በማን ትተማመናለህ? በምክርና በከንፈር ንግግር ጦርነት ይሆናልን? አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚያ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትል፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሥዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተስማማ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶችን እሰጥሃለሁ። ከታናናሾቹ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን ጭፍራ ፊት መመለስ እንዴት ትችላለህ? ስለ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በግብፅ የሚታመኑ ለጌታዬ ባሮች ናቸው። አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ እናጠፋችሁ ዘንድ ወደዚህ ሀገር ዘምተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደ ሀገራቸው ዘምታችሁ አጥፉአቸው” አለን። ኤልያቄምና ሳምናስ፥ ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። ራፋስቂስ ግን፥ “ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፥ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ለተቀመጡት ሰዎች እነግራቸው ዘንድ አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ በማይችል ቃል ሕዝቅያስ አያታልላችሁ። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድናችኋል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም አይበላችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በሕይወት ልትኖሩ ብትወድዱ ሁላችሁ ወደ እኔ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ትጠጣላችሁ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ አያታልላችሁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት ሀገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ ሀገሮች አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ አለን?” እነርሱም ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
ኢሳይያስ 36:4-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤ “ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው? የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ባዶ ቃል ብቻ ትናገራለህ። በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተደግፈህ ነው? እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብጽ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት! የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው። ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን? “ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ! የምትመካው በግብጽ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? ደግሞስ ይህን ምድር ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት ያለ እግዚአብሔር ይመስልሃልን? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ” ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ቃሎች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኵስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው። የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ‘ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ እርሱ ሊያድናችሁ አይችልምና!’ ደግሞም ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም’ እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋራ ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይኸውም፣ የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል የእንጀራና የወይን ምድር ወደሆነችው፣ እስካገባችሁ ድረስ ነው።’ “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት አያሳስታችሁ፤ ለመሆኑ፣ ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ከአሕዛብ አማልክት የትኛው ነው? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክትስ የት ደረሱ? እነዚህ ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ፣ አገሩን ከእጄ የታደገ የትኛው ነው? ታዲያ፣ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዴት ከእጄ ሊታደጋት ይችላል?” ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና።
ኢሳይያስ 36:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ራፋስቂስም አላቸው፦ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የሚትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? እኔ፦ ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃይልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፥ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፥ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ብቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር፦ ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ። ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን፦ እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባርያዎችህ ተናገር፥ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት። ራፋስቂስ ግን፦ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡ ሰዎች አይደለምን? አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፥ ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፥ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአልፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው? እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፥ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
ኢሳይያስ 36:4-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአሦር ባለ ሥልጣን የነበረው ራፋስ ቂስ እንዲህ አላቸው፦ “ለንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ‘እነሆ፥ የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፦ ለመሆኑ ይህን ያኽል ልበ ሙሉ የሆንከው በማን ተማምነህ ነው? ከንቱ ቃላት የጦርነት ስልትና ኀይል ይሆናል ብለህ ታስባለህን? ኧረ ለመሆኑ በእኔ ላይ ያመፅከው በማን ተማምነህ ነው? ምንአልባት ግብጽ ትረዳኛለች ብለህ ተስፋ አድርገህ ይሆናል፤ ነገር ግን በእርስዋ መታመን በሸምበቆ የመደገፍ ያኽል መሆኑን ዕወቀው፤ ተሰንጥሮ እጅህን ከሚወጋው በቀር ሸምበቆ ለምንም አይጠቅምህም፤ በግብጽ ንጉሥ የሚተማመንም የሚገጥመው ዕድል ይህንኑ የመሰለ ነው።’ ” የአሦራውያን ባለ ሥልጣን ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ ‘እኔ የምታመነው በአምላኬ በእግዚአብሔር ነው’ ትል ይሆናል፤ ታዲያ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚህ በአንድ መሠዊያ ብቻ እንዲያመልኩ ፈልገህ የእግዚአብሔርን መሠዊያዎችና የማምለኪያ ስፍራዎች ያፈራረስክ አንተ ሕዝቅያስ አይደለህምን? ስለዚህ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ስም ሆኜ የሚበጅህን ነገር እነግርሃለሁ፤ ተቀምጠውባቸው ለመጋለብ የሚደፍሩ ሰዎች ካሉህ ሁለት ሺህ ፈረሶችን እሰጥሃለሁ። አንተ ከአሦራውያን ባለሥልጣኖች የመጨረሻውን ዝቅተኛ መኰንን እንኳ ለመቋቋም የምትችል አይደለህም፤ ይህም ሆኖ ግብጻውያን ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ይልኩልኛል ብለህ ተስፋ ታደርጋለህ። እኔስ ብሆን ይህንን አገር ለመውረርና ለማጥፋት የቻልኩት ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ይመስልሃልን? እንዲያውም በአገሪቱ ላይ አደጋ ጥዬ እንዳጠፋት ያዘዘኝ እግዚአብሔር ራሱ ነው።” ከዚህ በኋላ ኤልያቄም፥ ሼብናና ዮአሕ የአሦራውያኑን ባለ ሥልጣን “እኛ ትርጒሙን ስለምናውቅ በሶርያ ቋንቋ እንድትነግረን እንለምንሃለን፤ በቅጽር ላይ ያሉት ሕዝብ ሁሉ በሚሰሙት በዕብራይስጥ ቋንቋ አትንገረን” አሉት። የአሦራውያን ባለሥልጣንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ የአሦር ንጉሥ ይህን ሁሉ ለእናንተና ለንጉሣችሁ ብቻ እንድናገር የላከኝ መሰላችሁን? ከቶ አይደለም፤ ልክ እንደ እናንተ ዐይነ ምድራቸውን መብላትና ሽንታቸውን መጠጣት ያለባቸው ሕዝቡም ጭምር ስለ ሆኑ እኔ የምናገረውን በቅጽሩ ላይ ያሉት ሕዝቡ ሁሉ እንዲሰሙት ነው።” ስለዚህ የአሦር ባለ ሥልጣን ከተቀመጠበት ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ እያለ መናገር ጀመረ፦ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ! በሕዝቅያስ አትታለሉ፤ እርሱ ሊያድናችሁ ከቶ አይችልም፤ ሕዝቅያስ ‘በእግዚአብሔር ተማመኑ፤ እርሱ ያድነናል፤ ከተማችንም በአሦራውያን ሠራዊት እጅ እንዳትገባ ይከላከልልናል’ እያለ የሚያግባባችሁን አትስሙት። ሕዝቅያስ የሚላችሁን አታዳምጡ! የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፦ ወደ እኔ ኑና ከእኔ ጋር ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ይህን ብታደርጉ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ የወይን ተክሎቻችሁን ዘለላ የበለስ ዛፎቻችሁን ፍሬ ትበላላችሁ፤ ከጒድጓዶቻችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ። ይህም የሚሆነው ንጉሡ የእናንተን አገር ወደምትመስል ምድር ወስዶ እስከሚያሰፍራችሁ ድረስ ነው፤ በዚያችም ምድር የወይን ጠጅ የሚገኝባቸው የወይን ተክል ቦታዎችና በቂ የእንጀራ እህል የሚመረትባቸው እርሻዎች አሉ፤ ስለዚህ ሕዝቅያስ ‘እግዚአብሔር ታደጋችኋል!’ እያለ በማሳሳት አያሞኛችሁ፤ ለመሆኑ ከሌሎች ሕዝቦች አማልክት መካከል አንድ እንኳ ከአሦር ንጉሥ እጅ አገሩን ለማዳን የቻለ ይገኛልን? ታዲያ ይህ ከሆነ የሀማትና የአርፋድ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዋይም አማልክትስ የት ደረሱ? ለመሆኑ ከእነርሱ አንዱ እንኳ ሰማርያን ከእጄ ሊያድን ችሎአልን? የእነዚህ ሁሉ አገሮች አማልክት ከእኔ እጅ አገራቸውን ለማዳን የቻሉበት ጊዜ አለን? ታዲያ እናንተ ‘እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድናታል’ ብላችሁ የምታስቡት እንዴት ነው?” ሕዝቡም ቀደም ሲል ንጉሥ ሕዝቅያስ ባዘዛቸው መሠረት አንዲት ቃል ሳይናገሩ ዝም አሉ።
ኢሳይያስ 36:4-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ራፋስቂስም እንዲህ አላቸው፦ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የምትተማመንበት መተማመኛ ምንድነው? ባዶ ቃል የጦር ስልትና ኃይል የሚሆንህ ይመስልህል? አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ የሸንበቆ በትር በግብጽ ተማምነሀል፤ ሰው ተማምኖ ቢመረኰዘው እጁን ወግቶ ያቈስለዋል፤ የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ ‘በአምላካችን በጌታ እንታመናለን’ ብትለኝ፥ ‘በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ’ ብሎ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ ያስፈረሰው እርሱ አይደለምን? እንግዲህ አሁን ናና፥ ከአለቃዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተደራደርና፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ካገኘህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከአለቃዬ ባርያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ለመቃወም እንዴት ይቻልሃል? አሁንም ቢሆን፥ ጌታ፦ ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ እንጂ፥ በውኑ ያለ ጌታ ይህን አገር ለማጥፋት የዘመትኩ ይመስልሃል?” ከዚያም ኤልያቄም፥ ሳምናስና ዮአስ ራፋስቂስን፦ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሚገባን በሶርያ ቋንቋ ለአገልጋዮችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ መግባቢያ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን” አሉት። ራፋስቂስ ግን፦ “አለቃዬ ይህን ቃል እንድናገር ወደ እናንተና ወደ አለቃችሁ ብቻ ልኮኛልን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኩስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ “የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ ሊያድናችሁ አይችልምና አያታላችሁ፤ ሕዝቅያስ፥ ጌታ በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም፥ ብሎ በጌታ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስን አትስሙ፤’ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ‘ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ኑ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጉድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስ፥ ጌታ ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋል? የሐማትና የአልፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታል? ጌታ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ፥ ከእነዚህ አገሮች ሁሉ አማልክት አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?’” እነርሱ ግን ዝም አሉ፥ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና “አንዳችም አልመለሱለትም”።