ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በማን ትተማመናለህ? በምክርና በከንፈር ንግግር ጦርነት ይሆናልን? አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚያ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትል፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሥዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተስማማ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶችን እሰጥሃለሁ። ከታናናሾቹ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን ጭፍራ ፊት መመለስ እንዴት ትችላለህ? ስለ ሰረገሎችና ፈረሰኞች በግብፅ የሚታመኑ ለጌታዬ ባሮች ናቸው። አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ እናጠፋችሁ ዘንድ ወደዚህ ሀገር ዘምተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደ ሀገራቸው ዘምታችሁ አጥፉአቸው” አለን። ኤልያቄምና ሳምናስ፥ ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። ራፋስቂስ ግን፥ “ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ፥ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ለተቀመጡት ሰዎች እነግራቸው ዘንድ አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ በማይችል ቃል ሕዝቅያስ አያታልላችሁ። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድናችኋል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም አይበላችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ በሕይወት ልትኖሩ ብትወድዱ ሁላችሁ ወደ እኔ ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ትጠጣላችሁ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ አያታልላችሁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት ሀገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ ሀገሮች አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ አለን?” እነርሱም ዝም አሉ፤ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
ትንቢተ ኢሳይያስ 36 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 36:4-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች