ኢሳይያስ 28:9-13
ኢሳይያስ 28:9-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክፉን ለማን ተናገርን? ወሬን ለማን አወራን? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? ሕማምን በሕማም ላይ፥ ተስፋንም በተስፋ ላይ ተቀበሉ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም፥ “ይህችም ለደከመ ዕረፍት ናት፤ ይህችም መቅሠፍት ናት፤” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ ተጠምደውም እንዲቸገሩ፥ የግዚአብሔርም ቃሉ በሕማም ላይ ሕማም፥ በተስፋ ላይ ተስፋ፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።
ኢሳይያስ 28:9-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እነርሱም እንዲህ ይላሉ፤ “የሚያስተምረው ማንን ነው? መልእክቱን የሚያብራራውስ ለማን ነው? ወተት ለተዉት ሕፃናት? ወይስ ጡት ለጣሉት? በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤ በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤ እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት ነውና።” እንግዲያው እግዚአብሔር፣ በባዕድ ልሳን በእንግዳ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል። እርሱ፣ “ይህች የዕረፍት ቦታ ናት፤ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህች የእፎይታ ቦታ ናት” ያለው ለማን ነበር? እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤ በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤ እዚህ ጥቂት እዚያ ጥቂት ይሆንባቸዋል። ይህ የሚሆንባቸው ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፣ እንዲቈስሉና በወጥመድ እንዲያዙ፣ እንዲማረኩም ነው።
ኢሳይያስ 28:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን? ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፥ እርሱም፦ ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፥ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፥ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።
ኢሳይያስ 28:9-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱ ማንን ለማስተማር ይፈልጋል? መልእክቱንስ የሚገልጠው ለማነው? የእርሱ ትምህርት የሚጠቅመው ጡት ለጣሉ ሕፃናት ብቻ አይደለም። እርሱ፦ ሊያስተምረን የሚሞክረው ፊደል በፊደል ላይ፥ መስመር በመስመር ላይ፥ ትምህርት በትምህርት ላይ እያነባበረ እንደ ጀማሪ እንድንንተባተብ ነው። እነሆ፥ እግዚአብሔር ይህንን ሕዝብ በአልተለመደ አነጋገርና በባዕድ ቋንቋ ይናገራል። ዕረፍትንና መጽናናትን ሰጥቶአችሁ ነበር፤ እናንተ ግን እርሱን ማዳመጥ እምቢ አላችሁ። እግዚአብሔር ፊደል በፊደል ላይ፥ መስመር በመስመር ላይ፥ ትምህርት በትምህርት ላይ እያነባበረ ሊያስተምራችሁ የፈቀደው ስለዚህ ነው፤ በዚያን ጊዜ በእርምጃችሁ ሁሉ ትሰናከላላችሁ፤ ትቈስላላችሁ፤ በወጥመድም ተይዛችሁ ትታሰራላችሁ።
ኢሳይያስ 28:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን?” በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው። በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም፦ “ዕረፍት ይህች ናት፥ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት” አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ። ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፥ እንዲሰበሩም፥ በወጥመድም እንዲያዙ፥ የጌታ ቃል በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፥ በደንብ ላይ ደንብ፥ በደንብ ላይ ደንብ፤ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።