ሆሴዕ 12:7-14
ሆሴዕ 12:7-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፤ ዘወትርም ወደ አምላክህ ቅረብ። በከነዓን እጅ የዐመፅ ሚዛን አለ፤ ቅሚያንም ይወድዳል። ኤፍሬምም፥ “ባለጸጋ ሆኜአለሁ፤ ሀብትንም አግኝቻለሁ፤ በድካሜም ሁሉ ኀጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም” አለ። እኔም ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀንም እንደ ገና በድንኳን አስቀምጥሃለሁ። ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፤ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ተመስያለሁ። በገለዓድ ባይሆንም እንኳ በጌልጌላ መሥዋዕታቸውን የሚሠዉ አለቆች ስተዋል፤ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ እንደ አለ የድንጋይ ክምር ነው። ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሀገር ሸሸ፤ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፤ ስለ ሚስትም ጠበቀ። እግዚአብሔርም በነቢይ እስራኤልን ከግብፅ ምድር አወጣው፤ በነቢይም ጠበቀው።
ሆሴዕ 12:7-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነጋዴው በሐሰተኛ ሚዛን ይሸጣል፤ ማጭበርበርንም ይወድዳል። ኤፍሬም እንዲህ እያለ ይታበያል፤ “እኔ ባለጠጋ ነኝ፤ ሀብታምም ሆኛለሁ፤ ይህ ሁሉ ሀብት እያለኝ፣ ምንም ዐይነት በደል ወይም ኀጢአት አያገኙብኝም።” “ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ በዓመት በዓላችሁ ቀን ታደርጉ እንደ ነበረው ሁሉ፣ እንደ ገና በድንኳኖች እንድትቀመጡ አደርጋችኋለሁ። ለነቢያት ተናገርሁ፤ ራእይንም አበዛሁላቸው፤ በእነርሱም በኩል በምሳሌ ተናገርሁ።” ገለዓድ ክፉ ነው? ሕዝቡም ከንቱ ናቸው! ኰርማዎችን በጌልገላ ይሠዋሉን? መሠዊያዎቻቸው በታረሰ መሬት ላይ እንዳለ፣ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ። ያዕቆብ ወደ ሶርያ ሸሸ፤ እስራኤል ሚስት ለማግኘት ሲል አገለገለ፤ ዋጋዋንም ለመክፈል በጎችን ጠበቀ። እግዚአብሔር በነቢይ አማካይነት እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፤ በነቢይም በኩል ተንከባከበው። ኤፍሬም ግን ክፉኛ አስቈጣው፤ ጌታውም የደም አፍሳሽነቱን በደል በላዩ ላይ ያደርግበታል፤ ስለ ንቀቱም የሚገባውን ይከፍለዋል።
ሆሴዕ 12:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፥ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን። ከከነዓን ወገን ነው፥ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል። ኤፍሬምም፦ ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም አለ። እኔም ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፥ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደ ገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ። ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፥ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን አውጥቻለሁ። ኃጢአት በገለዓድ አለ፥ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፥ ወይፈኖች በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ። ያዕቆብ ወደ ሶርያ አገር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም ጠባቂ ነበረ። እግዚአብሔርም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢያትም እጅ ጠበቀው።
ሆሴዕ 12:7-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ሐሰተኛ ሚዛን በእጃቸው እንደሚገኝ እንደ ከነዓናውያን ነጋዴዎች ሆነዋል፤ በእርሱም ያታልሉበታል፤ ‘እስራኤል እኔ ባለጸጋ ሆኛለሁ፤ በሀብቴም ማንም ሰው በእኔ ላይ በደል ወይም ኃጢአት አያገኝብኝም’ ብሎ ይፎክራል። ነገር ግን ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በዳስ በዓል ጊዜ በድንኳን እንደምትኖሩ ዐይነት፥ እንደገና ተመልሳችሁ በድንኳን እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። “አስቀድሜ በነቢያት አንደበት ተናግሬአለሁ፤ ብዙ ራእይም አሳይቻለሁ፤ በነቢያቱም አማካይነት በምሳሌ ተናግሬአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ በገለዓድ ለጣዖት ይሰግዳሉ፤ ለጣዖት የሚሰግዱት ግን ከንቱ ይሆናሉ፤ በጌልገላ ወይፈኖችን ለመሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ነገር ግን መሠዊያዎቻቸው ተሰባብረው በእርሻ መካከል የድንጋይ ክምር ሆነው ይቀራሉ።” የቀድሞ አባታችን ያዕቆብ ወደ መስጴጦምያ ሸሽቶ ሄደ፤ እዚያም ሚስት ለማግኘት ሲል የበጎች እረኛ ሆኖ አገለገለ። እግዚአብሔር በላከው ነቢይ አማካይነት የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ መርቶ አወጣቸው፤ በዚያም ነቢይ አማካይነት ተንከባከባቸው። ይሁን እንጂ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እጅግ አስቈጡት፤ በበደላቸውም ይጠየቁበታል፤ ስሙንም ስለ ሰደቡ ይፈርድባቸዋል።
ሆሴዕ 12:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ጽኑ ፍቅርንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን።” ከከነዓን ወገን ነው፤ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል። ኤፍሬምም፦ “በእውነት ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አያገኙብኝም” አለ። እኔም ጌታ፥ ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ። ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን ሰጥቻለሁ። ኃጢአት በገለዓድ አለ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፤ በሬዎችን በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልሞች ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ። ያዕቆብ ወደ አራም ምድር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም በጎችን ያሰማራ ነበረ። ጌታም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢያትም እጅ ጠበቀው።