ትንቢተ ሆሴዕ 12:7-14

ትንቢተ ሆሴዕ 12:7-14 አማ05

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እስራኤላውያን ሐሰተኛ ሚዛን በእጃቸው እንደሚገኝ እንደ ከነዓናውያን ነጋዴዎች ሆነዋል፤ በእርሱም ያታልሉበታል፤ ‘እስራኤል እኔ ባለጸጋ ሆኛለሁ፤ በሀብቴም ማንም ሰው በእኔ ላይ በደል ወይም ኃጢአት አያገኝብኝም’ ብሎ ይፎክራል። ነገር ግን ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በዳስ በዓል ጊዜ በድንኳን እንደምትኖሩ ዐይነት፥ እንደገና ተመልሳችሁ በድንኳን እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ። “አስቀድሜ በነቢያት አንደበት ተናግሬአለሁ፤ ብዙ ራእይም አሳይቻለሁ፤ በነቢያቱም አማካይነት በምሳሌ ተናግሬአለሁ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ በገለዓድ ለጣዖት ይሰግዳሉ፤ ለጣዖት የሚሰግዱት ግን ከንቱ ይሆናሉ፤ በጌልገላ ወይፈኖችን ለመሥዋዕት ያቀርባሉ፤ ነገር ግን መሠዊያዎቻቸው ተሰባብረው በእርሻ መካከል የድንጋይ ክምር ሆነው ይቀራሉ።” የቀድሞ አባታችን ያዕቆብ ወደ መስጴጦምያ ሸሽቶ ሄደ፤ እዚያም ሚስት ለማግኘት ሲል የበጎች እረኛ ሆኖ አገለገለ። እግዚአብሔር በላከው ነቢይ አማካይነት የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ መርቶ አወጣቸው፤ በዚያም ነቢይ አማካይነት ተንከባከባቸው። ይሁን እንጂ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን እጅግ አስቈጡት፤ በበደላቸውም ይጠየቁበታል፤ ስሙንም ስለ ሰደቡ ይፈርድባቸዋል።