ሆሴዕ 10:11-13
ሆሴዕ 10:11-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኤፍሬምም ቀንበርን እንደ ለመደች ጊደር ነው፤ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፤ ይሁዳንም እለጕመዋለሁ፤ ያዕቆብም ለራሱ መንግሥትን ያስተካክላል። ለእናንተ ጽድቅን ዝሩ፤ የሕይወት ፍሬን ሰብስቡ፤ የጥበብንም ብርሃን ለራሳችሁ አብሩ፤ የጽድቃችሁ መከር እስኪደርስ እግዚአብሔርን ፈልጉት። ዐመፅን ለምን ተከላችሁ? ኀጢአትንስ ለምን አጨዳችሁ፤ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በሠረገሎችህና በሠራዊትህ ብዛት ታምነሃል።
ሆሴዕ 10:11-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኤፍሬም ማበራየት እንደምትወድድ፣ እንደ ተገራች ጊደር ነው፤ በተዋበ ጫንቃዋም ላይ፣ ቀንበርን አኖራለሁ፤ ኤፍሬምን እጠምዳለሁ፤ ይሁዳ ያርሳል፤ ያዕቆብም መሬቱን ያለሰልሳል። ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና። እናንተ ግን ክፋትን ዘራችሁ፤ ኀጢአትንም ዐጨዳችሁ፤ የሐሰትንም ፍሬ በላችሁ። በራሳችሁ ጕልበት፣ በተዋጊዎቻችሁም ብዛት ታምናችኋልና፣
ሆሴዕ 10:11-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኤፍሬም ማበራየት እንደ ለመደች ጊደር ነው፥ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፥ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም አፈሩን ያለሰልሳል። እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ። ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፥ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።
ሆሴዕ 10:11-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“እስራኤል ማበራየት እንደምትወድ ጊደር ነበረች፤ ነገር ግን በተዋበ ጫንቃዋ ላይ ቀንበር እጭንበታለሁ፤ በዚህ ዐይነት ይሁዳ ያርሳል፤ የያዕቆብ ልጆች በሙሉ ተጠምደው መሬቱን ያለሰልሳሉ፤ እኔም ‘እንግዲህ ዕዳሪውን መሬት ዕረሱ፤ ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፤ የማይለዋወጥ ፍቅርን ሰብስቡ፤ እነሆ ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ የምትመለሱበት ጊዜ አሁን ነው! እኔም መጥቼ ፍትሕን አሰፍንላችኋለሁ’ አልኩ። “እናንተ ግን በራሳችሁ ኀይልና በጀግኖቻችሁ ብዛት በመተማመናችሁ፥ ክፋትን ዘርታችሁ ግፍን ሰበሰባችሁ፤ ሐሰታችሁ ያስገኘውን ፍሬ በላችሁ።
ሆሴዕ 10:11-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኤፍሬም ማበራየት የምትወድ የተገራች ጊደር ነበር፥ እኔም በውብ አንገትዋ ላይ አልጫንኩባትም፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፥ ይሁዳም ያርሳል፥ ያዕቆብም ለራሱ አፈሩን ያለሰልሳል። ጌታ መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የመሻት ዘመን ነውና ጽድቅን ለራሳችሁ ዝሩ፥ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ሰብስቡ፥ ያልታረሰ መሬታችሁን እረሱ። ክፋትን አርሳችኋል፥ ኃጢአትንም አጭዳችኋል፥ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በኃያላንህ ብዛት፥ በመንገድህም ላይ ታምነሃልና።