ዘፍጥረት 6:9-14
ዘፍጥረት 6:9-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ፥ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን፥ ካምን ያፌትንም ወለደ። ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተመላች። እግዚአብሔርም ምድርን እንደ ተበላሸች፥ ሥጋን የለበሱ ሁሉም በምድር ላይ መንገዳቸውን እንደ አበላሹ አየ። እግዚአብሔር አምላክም ኖኅን አለው፥ “የሰው ሁሉ ጊዜው በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተመልታለችና፤ እኔም እነሆ፥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ባለ አራት መዓዝን የዕንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ፤ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፤ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።
ዘፍጥረት 6:9-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው። ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋራ አደረገ። ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ። እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። አንተ ግን በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው።
ዘፍጥረት 6:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የኖኅ ትውልድ እንዲህ ነው። ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ስው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረግ። ኖኅም ሦስት ልጆችን ሴምን ካምን ያፌትንም ወለደ። ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸ ምድርም ግፍን ተሞላች። እግዚአብሔርም ምድርን አየ፤ እነሆም ተበላሸች ሥጋን የለበሰ ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበርና። እግዚእብሔርም ኖኅን አለው፤ የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችን እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ከጎፈር እንጨት መርከብን ለአንተ ሥራ በመርከቢቱም ጉርጆችን አድርግ በውስጥን በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።
ዘፍጥረት 6:9-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ምንም በደል የማይሠራና የእግዚአብሔርን መንገድ የሚከተል ደግ ሰው ነበር፤ ኖኅም ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። በዚያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉዎች ነበሩ፤ ምድርም በዐመፅ ተሞልታ ነበር። እግዚአብሔር ዓለምን ተመለከተ፤ የተበላሸች እንደ ሆነችና በውስጧም ያሉት ሰዎች ሁሉ በክፋት እንደሚኖሩ አየ። እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “የሰውን ዘር ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ምድር በሰዎች የዐመፅ ሥራ ስለ ተሞላች ሰዎችን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ፤ አንተ ግን ከጥሩ እንጨት መርከብ ሥራ፤ በውስጡም ብዙ ክፍሎች እንዲኖሩት አድርግ፤ መርከቡን ከውስጥና ከውጪ በቅጥራን ለቅልቀው።
ዘፍጥረት 6:9-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የኖኅ ትውልድ እንደሚከተለው ነው። ኖኅም ጻድቅ፥ በትውልዱም በደል ያልተገኘበት ሰው ነበረ፥ ኖኅም እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። ሴም፥ ካምና ያፌት የሚባሉትን ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። በዚያን ጊዜ ምድር በእግዚአብሔር ፊት የተበላሸች ነበረች፥ ምድርም ግፍን ተሞላች። እግዚአብሔርም ምድርን አየ፥ እነሆም፥ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በምድር ላይ መንገዳቸውን አበላሽተው ነበርና፥ ምድር የተበላሸች ነበረች። እግዚእብሔርም ኖኅን አለው፦ “የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ ደርሶአል፥ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተሞልታለችና፥ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ። ለአንተ ከጎፈር እንጨት መርከብን ሥራ፥ በመርከቢቱም ክፍሎችን አድርግ፥ በውስጥም፥ በውጭም በቅጥራን ለቅልቃት።