ዘፍጥረት 25:23-26
ዘፍጥረት 25:23-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማኅፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይወለዳሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።” የምትወልድበትም ወራት ተፈጸመ፤ በማኅፀንዋም መንታ ነበሩ። የበኵር ልጅዋም ወጣ፤ እንደ ጽጌረዳም ቀይ ነበረ፤ ሁለንተናውም ጠጕራም ነበር፤ ስሙንም ዔሳው ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙንም ያዕቆብ ብላ ጠራችው። ርብቃ ዔሳውንና ያዕቆብን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
ዘፍጥረት 25:23-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤ “ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት። የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀኗ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ። በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጕር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ። ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይሥሐቅ የስድሳ ዓመት ሰው ነበር።
ዘፍጥረት 25:23-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። ትወልድ ዘንድ ዘመንዋ በተፈጸመ ጊዜም እነሆ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንትናውም ጠጕር ለብሶ ነበር፤ ስሙም ዔሳው ተባለ። ከዚይም በኍላ ወንድሙ ወጣ በእጁም፥ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስሙም ያዕቆብ ተባለ። እርስዋ ልጆችን በወለደቻቸው ጊዜ ይስሐቅ ስድሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
ዘፍጥረት 25:23-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም፥ “በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደች። የመጀመሪያው ልጅ መልኩ ቀይ፥ ሰውነቱ ጠጒራም ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ተባለ። ሁለተኛው ልጅ ሲወለድ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ በመውጣቱ ያዕቆብ ተባለ፤ ልጆቹ በተወለዱ ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር።
ዘፍጥረት 25:23-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም እንዲህ አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንዱም ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።” የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ በማኅፀንዋ መንታ ነበሩ። በመጀመሪያም የወጣው ቀይ ነበረ፥ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር፥ ስለዚህ ዔሳው ብለው ጠሩት። ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ፥ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ልጆቹን በወለደች ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር።