ዘፀአት 24:13-18
ዘፀአት 24:13-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም ከኢያሱ ጋር ተነሣ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራም ወጡ። ሽማግሌዎችንም፥ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩን፤ ግርግር አትበሉ፤ አሮንና ሆርም እነሆ፥ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ” አላቸው። ሙሴም ከኢያሱ ጋር ወደ ተራራ ወጣ፤ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። በተራራውም ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ፤ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን፥ አርባ ሌሊትም ቈየ።
ዘፀአት 24:13-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋራ ዐብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ ክርክር ያለው ባለጕዳይ ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው። ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው። ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ክብር በተራራው ጫፍ ላይ እንደሚባላ እሳት ሆኖ ይታይ ነበር። ከዚያም ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ውስጥ ገባ፤ በተራራውም ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።
ዘፀአት 24:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። ሽማግሌዎችንም፦ ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው። ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።
ዘፀአት 24:13-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴና አገልጋዩ ኢያሱ ተዘጋጁ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ፤ ሙሴም ለመሪዎቹ “እንደገና ወደ እናንተ ተመልሰን እስክንመጣ በዚህ ቈዩን፤ አሮንና ሑርም እነሆ፥ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ ስለዚህም በመካከላችሁ ጥልና ክርክር ያለበት ሰው ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ” አላቸው። ሙሴም ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ተራራውንም ደመና ሸፈነው፤ የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ዐረፈ፤ ደመናውም ተራራውን ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። በተራራው ጫፍ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር በእስራኤል ሕዝብ ዘንድ እንደሚባላ እሳት ይታይ ነበር። ሙሴም ወጥቶ በተራራው ላይ ወዳለው ደመና ውስጥ ገባ፤ እዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።
ዘፀአት 24:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴና አገልጋዩ ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። ሽማግሌዎቹንም፦ “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሑርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ባለ ጉዳይም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ” አላቸው። ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። የጌታም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። በተራራው ራስ ላይ የጌታ ክብር ለእስራኤል ልጆች እንደሚባላ እሳት ሆኖ ታያቸው። ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቆየ።