አስቴር 8:1-10

አስቴር 8:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ዕለት ንጉሥ ጠረክሲስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ንብረት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤ አስቴርም መርዶክዮስ እንዴት እንደሚዛመዳት ለንጉሡ ነግራው ስለ ነበር፣ መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ቀረበ። ንጉሡ ከሐማ መልሶ የወሰደውን ባለማኅተም ቀለበት አውልቆ ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሐማ ቤት ንብረት ላይ ሾመችው። አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ ልመናዋን እንደ ገና አቀረበች። አጋጋዊው ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ክፉ ሤራ እንዲሽር ለመነችው። ከዚያም ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ለአስቴር ዘረጋላት፤ እርሷም ተነሥታ በፊቱ ቆመች። እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጕዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሠኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የዘመዶቼንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?” ንጉሥ ጠረክሲስም ለንግሥት አስቴርና ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እነሆ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ስላቀደ፣ ቤት ንብረቱን ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለውታል። በንጉሥ ስም የተጻፈና በቀለበቱ የታተመ ደብዳቤ ሊሻር ስለማይችል፣ እናንተ ደግሞ አይሁድን በተመለከተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሌላ ዐዋጅ በንጉሡ ስም ጽፋችሁ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐትሙት።” ኒሳን በተባለው በሦስተኛው ወር ሃያ ሦስተኛ ቀን የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊዎች በአስቸኳይ ተጠርተው ነበር፤ እነርሱም የመርዶክዮስን ትእዛዝ ሁሉ ለአይሁድ፣ እንዲሁም ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፣ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚገኙ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦችና መኳንንት ሁሉ ጻፉ። እነዚህም ትእዛዞች የተጻፉት በእያንዳንዱ አውራጃ ፊደልና በእያንዳንዱ ሕዝብ ቋንቋ፣ እንደዚሁም ለአይሁድ በገዛ ፊደላቸውና በገዛ ቋንቋቸው ነበር። መርዶክዮስ ትእዛዙን በንጉሥ ጠረክሲስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም ዐተመው፤ ከዚያም በተለይ ለንጉሡ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው።

አስቴር 8:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የአይሁድን ጠላት የሐማን ቤት ለንግሥቲቱ ለአስቴር ሰጠ። አስቴርም ለእርስዋ ምን እንደ ሆነ ነግራው ነበርና መርዶክዮስ ወደ ንጉሡ ፊት ገባ። ንጉሡም ከሐማ ያወለቀውን ቀለበቱን አወጣ፥ ለመርዶክዮስም ሰጠው። አስቴርም በሐማ ቤት ላይ መርዶክዮስን ሾመች። አስቴርም እንደ ገና በንጉሡ ፊት ተናገረች፥ በእግሩም ላይ ወድቃ እያለቀሰች የአጋጋዊውን የሐማን ክፋትና በአይሁድ ላይ የተተነኰለውን ተንኰል ይሽር ዘንድ ለመነችው። ንጉሡም የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፥ አስቴርም ተነሥታ በንጉሡ ፊት ቆመችና፦ ንጉሡን ደስ ቢያሰኘው፥ በፊቱም ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፥ ይህም ነገር በፊቱ ቅን ቢሆን፥ እኔም በእርሱ ዘንድ ተወድጄ እንደ ሆነ፥ አጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አገር ሁሉ ያሉትን አይሁድ ለማጥፋት የጻፈው ተንኰል ይገለበጥ ዘንድ ይጻፍ። እኔ በሕዝቤ ላይ የሚወርደውን ክፉ ነገር አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ወይስ የዘመዶቼን ጥፋት አይ ዘንድ እንዴት እችላለሁ? አለች። ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን፦ እነሆ የሐማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፥ እርሱም እጆቹን በአይሁድ ላይ ስለ ዘረጋ በግንድ ላይ ተሰቀለ። በንጉሡ ስም የተጻፈና በንጉሡ ቀለበት የታተመ አይገለበጥምና እናንተ ደግሞ ደስ የሚያሰኛችሁን በንጉሡ ስም ስለ አይሁድ ጻፉ፥ በንጉሡም ቀለበት አትሙ አላቸው። በዚያን ጊዜም ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሀያ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፥ መርዶክዮስም ስለ አይሁድ እንዳዘዘው ሁሉ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባቱ አገሮች ላሉ ሹማምትና አለቆች አዛውንትም ለእያንዳንዱም አገር እንደ ጽሕፈቱ ለእያንዳንዱም ሕዝብ እንደ ቋንቋው ለአይሁድም እንደ ጽሕፈታቸውና እንደ ቋንቋቸው ተጻፈ። በንጉሡም በአርጤክስስ ስም አስጻፈው፥ በንጉሡም ቀለበት አሳተመው፥ ደብዳቤውንም በንጉሡ ፈረስ ቤት በተወለዱት፥ ለንጉሡም አገልግሎት በተለዩ በፈጣን ፈረሶች በተቀመጡ መልእክተኞች እጅ ሰደደው።

አስቴር 8:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሥ አርጤክስስ የአይሁድ ጠላት የነበረውን የሃማንን ሀብት በሙሉ በዚያኑ ዕለት ለአስቴር ሰጣት፤ አስቴርም፥ መርዶክዮስ ለእርስዋ የቅርብ ዘመድ መሆኑን ለንጉሡ ነገረችው፤ መርዶክዮስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ ተፈቀደለት፤ ንጉሡም የራሱ ማኅተም ያለበትን፥ ከሃማን ጣት ወልቆ እንዲመለስ የተደረገውን ቀለበት ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሃማን ሀብትና ንብረት ላይ ኀላፊ አድርጋ ሾመችው። ከዚህም በኋላ አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ እንደገና አቤቱታዋን አቀረበች፤ የአጋግ ዘር የሆነው ሃማን በአይሁድ ላይ የቋጠረውን ክፉ ሤራ ለማቆም አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ለመነችው። ንጉሡም የወርቁን በትር ዘረጋላት፤ እርስዋም ተነሥታ በፊቱ በመቆም እንዲህ አለች፤ “የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ቢሆንና ስለ እኔም የሚያስብልኝ ከሆነ፥ እንዲሁም ጉዳዩ በእርስዎ ፊት ትክክል ሆኖ ከተገኘ፥ በንጉሠ ነገሥት ግዛትዎ ሁሉ ውስጥ የሚገኙ አይሁድ ሁሉ ይደመሰሱ ዘንድ የአጋግ ዘር የነበረው የሃመዳታ ልጅ ሃማን ሰጥቶት የነበረውን ትእዛዝ ሁሉ የሚሽር ዐዋጅ እንዲያስተላልፉልኝ እለምንሃለሁ። ይህ ሁሉ ጥፋት በሕዝቤ ላይ ሲደርስና የገዛ ዘመዶቼም ሲገደሉ እንዴት መታገሥ እችላለሁ?” ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ሃማን በአይሁድ ላይ ስለ ፈጸመው ሤራ በእንጨት ላይ እንዳሰቀልኩትና ሀብቱንም ሁሉ ለአስቴር እንደ ሰጠሁ የሚታወስ ነው፤ ይሁን እንጂ የቤተ መንግሥቱ ማኅተም ያለበትና በንጉሡ ስም የተላለፈ ዐዋጅ ሊለወጥ አይችልም፤ ሆኖም እናንተ በበኩላችሁ የፈለጋችሁትን ነገር ለአይሁድ ጻፉላቸው፤ በእኔም ስም ከጻፋችሁ በኋላ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አትሙበት።” ይህም የሆነው ሲዋን ተብሎ የሚጠራው ሦስተኛ ወር በገባ በሃያ ሦስተኛው ቀን ነበር፤ መርዶክዮስ የንጉሡን ጸሐፊዎች ሁሉ ጠርቶ ለአይሁድ፥ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮች ለሚያስተዳድሩ አገረ ገዢዎችና ሌሎችም ባለሥልጣኖች የሚላኩ ደብዳቤዎችን አስጻፈ፤ ደብዳቤዎቹም በእያንዳንዱ አገር ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት እንዲሁም በአይሁድ ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትለው እንዲጻፉ ተደረገ። መርዶክዮስ ደብዳቤዎቹን ሁሉ በንጉሥ አርጤክስስ ስም አስጽፎ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አተመባቸው፤ ደብዳቤዎቹም በቤተ መንግሥቱ ጋጥ በተቀለቡ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ ጋላቢዎች እጅ እንዲላኩ አደረገ።