መጽሐፈ አስቴር 8:1-10

መጽሐፈ አስቴር 8:1-10 አማ05

ንጉሥ አርጤክስስ የአይሁድ ጠላት የነበረውን የሃማንን ሀብት በሙሉ በዚያኑ ዕለት ለአስቴር ሰጣት፤ አስቴርም፥ መርዶክዮስ ለእርስዋ የቅርብ ዘመድ መሆኑን ለንጉሡ ነገረችው፤ መርዶክዮስም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወደ ንጉሡ ፊት መቅረብ ተፈቀደለት፤ ንጉሡም የራሱ ማኅተም ያለበትን፥ ከሃማን ጣት ወልቆ እንዲመለስ የተደረገውን ቀለበት ለመርዶክዮስ ሰጠው፤ አስቴርም መርዶክዮስን በሃማን ሀብትና ንብረት ላይ ኀላፊ አድርጋ ሾመችው። ከዚህም በኋላ አስቴር በንጉሡ እግር ላይ ወድቃ በማልቀስ እንደገና አቤቱታዋን አቀረበች፤ የአጋግ ዘር የሆነው ሃማን በአይሁድ ላይ የቋጠረውን ክፉ ሤራ ለማቆም አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ለመነችው። ንጉሡም የወርቁን በትር ዘረጋላት፤ እርስዋም ተነሥታ በፊቱ በመቆም እንዲህ አለች፤ “የግርማዊነትዎ መልካም ፈቃድ ቢሆንና ስለ እኔም የሚያስብልኝ ከሆነ፥ እንዲሁም ጉዳዩ በእርስዎ ፊት ትክክል ሆኖ ከተገኘ፥ በንጉሠ ነገሥት ግዛትዎ ሁሉ ውስጥ የሚገኙ አይሁድ ሁሉ ይደመሰሱ ዘንድ የአጋግ ዘር የነበረው የሃመዳታ ልጅ ሃማን ሰጥቶት የነበረውን ትእዛዝ ሁሉ የሚሽር ዐዋጅ እንዲያስተላልፉልኝ እለምንሃለሁ። ይህ ሁሉ ጥፋት በሕዝቤ ላይ ሲደርስና የገዛ ዘመዶቼም ሲገደሉ እንዴት መታገሥ እችላለሁ?” ከዚህም በኋላ ንጉሥ አርጤክስስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ ሃማን በአይሁድ ላይ ስለ ፈጸመው ሤራ በእንጨት ላይ እንዳሰቀልኩትና ሀብቱንም ሁሉ ለአስቴር እንደ ሰጠሁ የሚታወስ ነው፤ ይሁን እንጂ የቤተ መንግሥቱ ማኅተም ያለበትና በንጉሡ ስም የተላለፈ ዐዋጅ ሊለወጥ አይችልም፤ ሆኖም እናንተ በበኩላችሁ የፈለጋችሁትን ነገር ለአይሁድ ጻፉላቸው፤ በእኔም ስም ከጻፋችሁ በኋላ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አትሙበት።” ይህም የሆነው ሲዋን ተብሎ የሚጠራው ሦስተኛ ወር በገባ በሃያ ሦስተኛው ቀን ነበር፤ መርዶክዮስ የንጉሡን ጸሐፊዎች ሁሉ ጠርቶ ለአይሁድ፥ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ያሉትን መቶ ኻያ ሰባት አገሮች ለሚያስተዳድሩ አገረ ገዢዎችና ሌሎችም ባለሥልጣኖች የሚላኩ ደብዳቤዎችን አስጻፈ፤ ደብዳቤዎቹም በእያንዳንዱ አገር ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት እንዲሁም በአይሁድ ቋንቋና የአጻጻፍ ሥርዓት ተከትለው እንዲጻፉ ተደረገ። መርዶክዮስ ደብዳቤዎቹን ሁሉ በንጉሥ አርጤክስስ ስም አስጽፎ የቤተ መንግሥቱን ማኅተም አተመባቸው፤ ደብዳቤዎቹም በቤተ መንግሥቱ ጋጥ በተቀለቡ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ ጋላቢዎች እጅ እንዲላኩ አደረገ።