አሞጽ 1:1-15

አሞጽ 1:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በቴ​ቁሔ በላም ጠባ​ቂ​ዎች መካ​ከል የነ​በረ አሞጽ በይ​ሁዳ ንጉሥ በዖ​ዝ​ያን ዘመን፥ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ በዮ​አስ ልጅ በኢ​ዮ​ር​ብ​ዓም ዘመን፥ የም​ድር መና​ወጥ ከሆ​ነ​በት ከሁ​ለት ዓመት በፊት ስለ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ያየው ቃል ይህ ነው። እን​ዲ​ህም አለ፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከጽ​ዮን ሆኖ ድም​ፁን ከፍ አድ​ርጎ ይና​ገ​ራል፤ ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ሆኖ ቃሉን ይሰ​ጣል፤ የእ​ረ​ኞ​ችም ማሰ​ማ​ሪ​ያ​ዎች ያለ​ቅ​ሳሉ፤ የቀ​ር​ሜ​ሎ​ስም ራስ ይደ​ር​ቃል።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “የገ​ለ​ዓ​ድን ነፍሰ ጡሮች በብ​ረት መጋዝ ሰን​ጥ​ቀ​ዋ​ቸ​ዋ​ልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደ​ማ​ስቆ ኀጢ​አት መቅ​ሠ​ፍ​ቴን ከማ​ድ​ረግ አል​መ​ለ​ስ​ላ​ቸ​ውም። በአ​ዛ​ሄል ቤት ላይ እሳ​ትን እሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ የወ​ልደ አዴ​ር​ንም መሠ​ረ​ቶች ትበ​ላ​ለች። የደ​ማ​ስ​ቆ​ንም ቍል​ፎች እሰ​ብ​ራ​ለሁ፤ በአ​ዎን ሸለቆ የሚ​ኖ​ሩ​ት​ንም ሰዎች አጠ​ፋ​ለሁ፤ የካ​ራን ሰዎች ወገ​ኖ​ች​ንም እቈ​ራ​ር​ጣ​ለሁ፤ የሶ​ርያ ሕዝ​ብም ወደ ቂር ይማ​ረ​ካሉ፤” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “በኤ​ዶ​ም​ያስ ይዘ​ጉ​ባ​ቸው ዘንድ የሰ​ሎ​ሞ​ንን ምርኮ ማር​ከ​ዋ​ልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኀጢ​አት መቅ​ሠ​ፍ​ቴን ከማ​ድ​ረግ አል​መ​ለ​ስ​ላ​ቸ​ውም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳ​ትን እሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ መሠ​ረ​ቶ​ች​ዋ​ንም ትበ​ላ​ለች። የአ​ዛ​ጦን ነዋ​ሪ​ዎ​ችን አጠ​ፋ​ለሁ፤ የአ​ስ​ቀ​ሎ​ናም ሕዝብ ይጠ​ፋ​ለሁ፤ እጄ​ንም በአ​ቃ​ሮን ላይ እመ​ል​ሳ​ለሁ፤ ከፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን የቀ​ሩ​ትም ይጠ​ፋሉ” ይላል ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “የሰ​ሎ​ሞን ምር​ኮ​ኞ​ችን በኤ​ዶ​ም​ያስ ዘግ​ተ​ዋ​ልና፥ የወ​ን​ድ​ሞ​ች​ንም ቃል ኪዳን አላ​ሰ​ቡ​ምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢ​ሮስ ኀጢ​አት አል​መ​ለ​ስ​ላ​ቸ​ውም። በጢ​ሮስ ቅጥር ላይ እሳ​ትን አሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ መሠ​ረ​ቶ​ች​ዋ​ንም ትበ​ላ​ለች።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፦“ወን​ድ​ሙን በሰ​ይፍ አሳ​ድ​ዶ​ታ​ልና፥ በም​ድር ላይም ማኅ​ፀ​ንን አር​ክ​ሶ​አ​ልና፥ የሚ​ዘ​ል​ፈ​ው​ንና የሚ​ያ​ስ​ደ​ነ​ግ​ጠ​ውን በር​ብ​ሮ​አ​ልና፥ መዓ​ቱ​ንም ለዘ​ለ​ዓ​ለም ጠብ​ቆ​አ​ልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤ​ዶ​ም​ያስ ኀጢ​አት መቅ​ሠ​ፍ​ቴን ከማ​ድ​ረግ አል​መ​ለ​ስ​ላ​ቸ​ውም። በቴ​ማን ላይ እሳ​ትን እሰ​ድ​ዳ​ለሁ፤ የቅ​ጥ​ር​ዋ​ንም መሠ​ረ​ቶች ትበ​ላ​ለች።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “ዳር​ቻ​ቸ​ውን ያሰፉ ዘንድ የገ​ለ​ዓ​ድን ነፍሰ ጡሮች ቀድ​ደ​ዋ​ልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአ​ሞን ልጆች ኀጢ​አት መቅ​ሠ​ፍ​ቴን ከማ​ድ​ረግ አል​መ​ለ​ስም። በራባ ቅጥር ላይ እሳ​ትን አነ​ድ​ዳ​ለሁ፤ በጦ​ር​ነት ቀን በጩ​ኸት መሠ​ረ​ቶ​ች​ዋን ትበ​ላ​ለች፤ በፍ​ጻ​ሜ​ዋም ቀን ትና​ወ​ጣ​ለች። ንጉ​ሦ​ቻ​ቸ​ውን፥ አለ​ቆ​ቻ​ቸ​ው​ንና ካህ​ኖ​ቻ​ቸ​ውን በአ​ን​ድ​ነት ይማ​ር​ኳ​ቸ​ዋል፥” ይላል እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር።

አሞጽ 1:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በቴቁሔ ከነበሩት እረኞች መካከል አንዱ የሆነው አሞጽ፣ ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንዲሁም የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ በነበረ ጊዜ፣ ይኸውም የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየውና የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ከጽዮን ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማል፤ ከኢየሩሳሌምም ያንጐደጕዳል፤ የእረኞች ማሰማሪያዎች ደርቀዋል፤ የቀርሜሎስም ዐናት ጠውልጓል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የደማስቆ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የብረት ጥርስ ባለው ማሄጃ፣ ገለዓድን አሂዳለችና፤ የቤን ሃዳድ ምሽጎች እንዲበላ፣ በአዛሄል ቤት ላይ እሳት እሰድዳለሁ። የደማስቆን በሮች እሰባብራለሁ፤ በቤት ዔደን በትር የያዘውን፣ በአዌን ሸለቆ ያለውን ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርኮ ወደ ቂር ይሄዳል” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጋዛ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ በመውሰድ፣ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጋዛ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ። በአስቀሎና በትር የያዘውን፣ የአሽዶድንም ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ በፍልስጥኤም ካሉት የመጨረሻው ሰው እስኪሞት ድረስ፣ እጄን በአቃሮን ላይ እዘረጋለሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጢሮስ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም። የወንድማማችነትን ቃል ኪዳን በማፍረስ፣ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጢሮስ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የኤዶም ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ርኅራኄን በመንፈግ፣ ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፤ የቍጣውንም ነበልባል ሳይገድብ፣ መዓቱን ሳያቋርጥ አውርዶበታልና፤ የባሶራን ምሽጎች እንዲበላ፣ በቴማን ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የአሞን ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ድንበሩን ለማስፋት፣ የገለዓድን ነፍሰ ጡር ሴቶች ሆድ ቀድዷልና። በጦርነት ቀን በጩኸት ውስጥ፣ በማዕበል ቀን በዐውሎ ነፋስ ውስጥ፣ ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በረባት ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ። ንጉሧ ከሹማምቱ ጋራ፣ በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፣” ይላል እግዚአብሔር።

አሞጽ 1:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በቴቁሔ ከላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበቱ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ቃል ይህ ነው። እንዲህም አለ፦ እግዚአብሔር በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፥ የእረኞችም ማሰማርያዎች ያለቅሳሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ገለዓድን በብረት መንኰራኵር አሂዶአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄል ቤት እሳትን እሰድዳለሁ፥ የወልደ አዴርንም አዳራሾች ትበላለች። የደማስቆንም መወርወሪያ እሰብራለሁ፥ ተቀማጮችንም ከአዌን ሸለቆ አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፥ የሶርያም ሕዝብ ወደ ቂር ይማርካል፥ ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለኤዶምያስ አሳልፈው ይሰጡአቸው ዘንድ ምርኮኞችን ሁሉ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። ተቀማጮችን ከአዛጦን አጠፋለሁ፥ በትር የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፥ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምርኮኞችን ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ አዳራሾችዋንም ትበላለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄንም ሁሉ ጥሎአልና፥ ቍጣውም ሁልጊዜ ቀድዶአልና፥ መዓቱንም ለዘላለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፥ የባሶራንም አዳራሾች ትበላለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን እርጕዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኃጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ በሰልፍም ቀን በጩኸት በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት አዳራሾችዋን ትበላለች፥ ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ይማረካል፥ ይላል እግዚአብሔር።

አሞጽ 1:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዖዝያን በይሁዳ፥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓምም በእስራኤል ላይ በነገሡበት ዘመን፥ በተቆዓ ከሚገኙ እረኞች አንዱ የሆነው አሞጽ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው። አሞጽ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ሆኖ እንደሚያገሣ አንበሳ የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤ ቃሉም ከኢየሩሳሌም ያስተጋባል፤ እረኞች መንጋ የሚያሰማሩበት መስክ ይጠወልጋል፤ በቀርሜሎስ ተራራ የሚገኘውም ልምላሜ ይደርቃል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የደማስቆ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የገለዓድን ሕዝብ የብረት ጥርስ ባለው መንኰራኲር አበራይተው አሠቃይተዋቸዋል። በንጉሥ ሐዛኤል ቤተ መንግሥት ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ እሳቱም ንጉሥ ቤንሀዳድ የሠራቸውንም ምሽጎች ያቃጥላል። የደማስቆን ከተማ የቅጽር በር መዝጊያ ሁሉ እሰባብራለሁ፤ በአዌን ሸለቆ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የቤትዔደንን መሪ አስወግዳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይወሰዳሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የጋዛ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የሀገሩን ሕዝብ ሁሉ ከማረኩ በኋላ ለኤዶም ሰዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። ስለዚህ በጋዛ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ በአሽዶድ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የአስቀሎናን መሪ አጠፋለሁ፤ የዔቅሮን ከተማ ኗሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የተረፉትም ፍልስጥኤማውያን ይሞታሉ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የጢሮስ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ የገቡበትን የወንድምነት ቃል ኪዳን አፍርሰው የማረኳቸውን ሕዝቦች ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል፤ ስለዚህ በጢሮስ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኤዶም ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን በሰይፍ አሳደዋቸዋል፤ ከያዙአቸውም በኋላ ርኅራኄ አላደረጉላቸውም፤ በእነርሱ ላይ ያላቸው ቊጣ ሊበርድም አልቻለም፤ ስለዚህ በቴማን ከተማ ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የቦጽራንም ምሽጎች ያቃጥላል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዐሞን ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ግዛት ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ በገለዓድ የሚኖሩትን እርጉዞች ሴቶች እንኳ ሆዳቸውን ቀደዋል። ስለዚህ በራባ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ ከዚህ በኋላ በጦርነቱ ቀን ጩኸትና ሁካታ ይበዛል፤ ጦርነቱም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይፈጥናል፤ ንጉሣቸውና መሳፍንቱ ተማርከው ይሄዳሉ።”

አሞጽ 1:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የአሞጽ ቃላት፥ በቴቁሔ ከሚገኙ ከበግ አርቢዎች መካከል የነበረ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ይህ ነው። እንዲህም አለ፦ “ጌታ በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ድምፁን ያስተጋባል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ይጠወልጋሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ገለዓድን የብረት ጥርስ ባለው መውቅያ አበራይተውታልና ስለ ሦስት የደማስቆ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄልም ቤት ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የአዴርንም ልጅ የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። የደማስቆንም መቀርቀሪያ እሰብራለሁ፥ ነዋሪዎችዋንም ከአዌን ሸለቆ፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይሄዳሉ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ለኤዶምያስ አሳልፈው ለመስጠት መላውን ሕዝብ ማርከው ወስደዋልና ስለ ሦስት የጋዛ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። ነዋሪዎችዋን ከአዛጦን፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በምርኮ የሄዱትን ሕዝብ ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድማማቾችንም ቃል ኪዳን አላስታወሱምና ስለ ሦስት የጢሮስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄውንም ሁሉ አጥፍቷልና፥ ባለማቋረጥም ተቆጥቷልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት የኤዶምያስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በቴማን ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የባሶራንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ዳርቻቸውን ለማስፋት ሲሉ የገለዓድን እርጉዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት የአሞን ልጆች ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነዳለሁ፤ በጦርነትም ቀን በጩኸት፥ በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት የእርሷን የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፥” ይላል ጌታ።