ትንቢተ አሞጽ 1:1-15

ትንቢተ አሞጽ 1:1-15 መቅካእኤ

የአሞጽ ቃላት፥ በቴቁሔ ከሚገኙ ከበግ አርቢዎች መካከል የነበረ፥ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየው ይህ ነው። እንዲህም አለ፦ “ጌታ በጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፥ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ድምፁን ያስተጋባል፤ የእረኞችም ማሰማርያዎች ይጠወልጋሉ፥ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ገለዓድን የብረት ጥርስ ባለው መውቅያ አበራይተውታልና ስለ ሦስት የደማስቆ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በአዛሄልም ቤት ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የአዴርንም ልጅ የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። የደማስቆንም መቀርቀሪያ እሰብራለሁ፥ ነዋሪዎችዋንም ከአዌን ሸለቆ፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከዔደን ቤት አጠፋለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይሄዳሉ፥” ይላል ጌታ። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ለኤዶምያስ አሳልፈው ለመስጠት መላውን ሕዝብ ማርከው ወስደዋልና ስለ ሦስት የጋዛ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች። ነዋሪዎችዋን ከአዛጦን፥ በትረ መንግሥት የያዘውንም ከአስቀሎና አጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፥ ከፍልስጥኤማውያንም የቀሩት ይጠፋሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “በምርኮ የሄዱትን ሕዝብ ሁሉ ለኤዶምያስ አሳልፈው ሰጥተዋልና፥ የወንድማማቾችንም ቃል ኪዳን አላስታወሱምና ስለ ሦስት የጢሮስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የእርሷንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ ርኅራኄውንም ሁሉ አጥፍቷልና፥ ባለማቋረጥም ተቆጥቷልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት የኤዶምያስ ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በቴማን ላይ እሳትን እልካለሁ፥ የባሶራንም የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች።” ጌታ እንዲህ ይላል፦ “ዳርቻቸውን ለማስፋት ሲሉ የገለዓድን እርጉዞች ቀድደዋልና ስለ ሦስት የአሞን ልጆች ኃጢአት ስለ አራትም መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። በረባት ቅጥር ላይ እሳትን አነዳለሁ፤ በጦርነትም ቀን በጩኸት፥ በዐውሎ ነፋስም ቀን በሁከት የእርሷን የንጉሥ ቅጥሮች ትበላለች፤ ንጉሣቸውም ከአለቆቹ ጋር በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፥” ይላል ጌታ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}