ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 - Compare All Versions

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ጴጥ​ሮ​ስና ዮሐ​ን​ስም በዘ​ጠኝ ሰዓት ለጸ​ሎት በአ​ን​ድ​ነት ወደ ቤተ መቅ​ደስ ወጡ። ከእ​ናቱ ማኅ​ፀ​ንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተ​ወ​ለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅ​ደ​ስም ከሚ​ገ​ቡት ምጽ​ዋት ይለ​ምን ዘንድ ሁል​ጊዜ እየ​ተ​ሸ​ከሙ መል​ካም በሚ​ል​ዋት በመ​ቅ​ደስ ደጃፍ ያስ​ቀ​ም​ጡት ነበር። ጴጥ​ሮ​ስ​ንና ዮሐ​ን​ስ​ንም ወደ መቅ​ደስ ሲገቡ አይቶ ምጽ​ዋት ይሰ​ጡት ዘንድ ለመ​ና​ቸው። ጴጥ​ሮ​ስም ከዮ​ሐ​ንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመ​ለ​ከ​ተው፥ “ወደ እኛ ተመ​ል​ከት” አለው፤ ወደ እነ​ር​ሱም ተመ​ለ​ከተ፤ ምጽ​ዋት እን​ደ​ሚ​ሰ​ጡ​ትም ተስፋ አድ​ርጎ ነበር። ጴጥ​ሮ​ስም፥ “ወር​ቅና ብር የለ​ኝም፤ ያለ​ኝን ግን እሰ​ጥ​ሃ​ለሁ፤ እነሆ፥ በና​ዝ​ሬቱ በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ስም ተነ​ሥ​ተህ ሂድ” አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስ​ነ​ሣው፤ ያን​ጊ​ዜም እግ​ሩና ቍር​ጭ​ም​ጭ​ምቱ ጸና። ዘሎም ቆመ፤ እየ​ሮ​ጠና እየ​ተ​ራ​መ​ደም ሄደ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም እያ​መ​ሰ​ገነ ከእ​ነ​ርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅ​ደስ ገባ። ሕዝ​ቡም ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እያ​መ​ሰ​ገነ ሲመ​ላ​ለስ አዩት። እር​ሱም መል​ካም በም​ት​ባ​ለው በመ​ቅ​ደስ ደጃፍ ተቀ​ምጦ ምጽ​ዋት ይለ​ምን የነ​በ​ረው እንደ ሆነ ዐወ​ቁት፤ በእ​ር​ሱም ከሆ​ነው የተ​ነሣ መገ​ረ​ምና መደ​ነቅ ሞላ​ባ​ቸው። ጴጥ​ሮ​ስና ዮሐ​ን​ስም ይዘ​ውት ወደ መቅ​ደስ ሲገቡ ሕዝቡ ሁሉ ደን​ግ​ጠው ወደ ሰሎ​ሞን መመ​ላ​ለሻ ወደ እነ​ርሱ ሮጡ። ጴጥ​ሮ​ስም ሕዝ​ቡን ባያ​ቸው ጊዜ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እና​ንት የእ​ስ​ራ​ኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ለምን ታደ​ን​ቃ​ላ​ችሁ? እኛ​ንስ በኀ​ይ​ላ​ች​ንና በጽ​ድ​ቃ​ችን ይህን ሰው በእ​ግሩ እን​ዲ​ሄድ እን​ዳ​ደ​ረ​ግ​ነው አስ​መ​ስ​ላ​ችሁ ለምን ታዩ​ና​ላ​ችሁ? የአ​ብ​ር​ሃም አም​ላክ የይ​ስ​ሐቅ አም​ላክ፥ የያ​ዕ​ቆብ አም​ላክ፥ የአ​ባ​ቶ​ቻ​ች​ንም አም​ላክ፥ እና​ንተ አሳ​ል​ፋ​ችሁ የሰ​ጣ​ች​ሁ​ትን፥ እር​ሱም ሊተ​ወው ወዶ ሳለ በጲ​ላ​ጦስ ፊት የካ​ዳ​ች​ሁ​ትን ልጁን ኢየ​ሱ​ስን ገለ​ጠው። እና​ንተ ግን ቅዱ​ሱ​ንና ጻድ​ቁን ካዳ​ች​ሁት፤ ነፍሰ ገዳ​ዩን ሰውም እን​ዲ​ያ​ድ​ን​ላ​ችሁ ለመ​ና​ችሁ። የሕ​ይ​ወ​ትን ባለ​ቤት ግን ገደ​ላ​ች​ሁት፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከሙ​ታን ለይቶ አስ​ነ​ሣው፤ ለዚ​ህም እኛ ምስ​ክ​ሮቹ ነን። ስሙን በማ​መን ይህን የም​ታ​ዩ​ት​ንና የም​ታ​ው​ቁ​ትን የእ​ርሱ ስም አጸ​ናው፤ እር​ሱ​ንም በማ​መን በፊ​ታ​ችሁ ይህን ሕይ​ወት ሰጠው። “አሁ​ንም ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ አለ​ቆ​ቻ​ችሁ እን​ዳ​ደ​ረጉ ይህን ባለ​ማ​ወቅ እን​ዳ​ደ​ረ​ጋ​ች​ሁት አው​ቃ​ለሁ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን ክር​ስ​ቶስ መከ​ራን እን​ዲ​ቀ​በል በነ​ቢ​ያት ሁሉ አፍ አስ​ቀ​ድሞ እንደ ተና​ገረ እን​ዲሁ ፈጸመ። እን​ግ​ዲህ ኀጢ​አ​ታ​ችሁ ይሰ​ረ​ይ​ላ​ችሁ ዘንድ ንስሓ ግቡ፥ ተመ​ለ​ሱም። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘን​ድም የይ​ቅ​ርታ ዘመን ይመ​ጣል። አስ​ቀ​ድሞ የመ​ረ​ጠ​ው​ንም ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን ይል​ክ​ላ​ች​ኋል።

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ፣ ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋራ ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስኪ ወደ እኛ ተመልከት!” አለው። ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት ዐስቦ በትኵረት ተመለከታቸው። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤ ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቍርጭምጭሚቱ በረታ፤ ዘልሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋራ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣ ይህ ሰው ቀደም ሲል “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ። የተፈወሰውም ሰው ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋራ ጥብቅ ብሎ ዐብሯቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደ ነበሩበት “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ። ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቍጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ? የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በርሱ ፊት ካዳችሁት፤ ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤ የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን። ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው። “አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን የርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሟል። እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን፣ እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል።

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኵር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ፦ “ወደ እኛ ተመልከት” አለው። እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን፦ “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና፥ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፥ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ መልካምም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደ ሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፥ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፥ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፥ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞም በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም።

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፤ እዚያ “ውብ” እየተባለ የሚጠራ በር ነበር፤ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የሆነውን አንድ ሰው ሰዎች በየቀኑ እያመጡ እዚያ ያስቀምጡት ነበር፤ እርሱ እዚያ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት ይለምን ነበር። ይህ ሰው ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። እነርሱም ሰውየውን ትኲር ብለው አዩትና ጴጥሮስ “ወደ እኛ ተመልከት!” አለው። እርሱም ምጽዋት የሚሰጡት መስሎት ትኲር ብሎ አያቸው። ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥና ተራመድ!” አለው። ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውኑ እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ። ብድግ ብሎም ቆመ፤ እየተራመደም ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ እየተራመደና እየዘለለም እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። ሰዎቹም ሁሉ ሲራመድና እግዚአብሔርን ሲያመሰግን አዩት። “ውብ በር” እየተባለ በሚጠራው በቤተ መቅደሱ በር አጠገብ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይም በተደረገው ነገር ይገረሙና ይደነቁ ጀመር። የዳነው ሰው ከጴጥሮስና ከዮሐንስ አልለይም በማለት ይዞአቸው ሳለ ሰዎቹ ተደንቀው “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደሚባለው ስፍራ ወደ እነርሱ ሮጠው ሄዱ፤ ጴጥሮስም ሰዎቹን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ነገር ስለምን ትደነቃላችሁ? ስለምንስ ትኲር ብላችሁ ታዩናላችሁ? እኛ በራሳችን ኀይል ወይም በራሳችን መልካም ሥራ ይህን ሰው እንዲራመድ ያደረግነው ይመስላችኋልን? የአባቶቻችን የአብርሃም፥ የይስሐቅና፥ የያዕቆብ አምላክ ልጁን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እርሱን በጲላጦስ ፊት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስም ሊለቀው ቢፈልግ እንኳ ‘አንፈልግም’ አላችሁ። እናንተ ቅዱሱንና ጻድቁን ‘አንፈልገውም’ ብላችሁ አንድ ነፍሰ ገዳይ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ። ሕይወት ሰጪ የሆነውንም ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን። ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው ድኖ የበረታው በኢየሱስ ስም በተገኘው እምነት ነው፤ በኢየሱስ ስም በማመኑም በሁላችሁ ፊት ሙሉ ጤንነት አግኝቶአል። “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ! በኢየሱስ ላይ ያደረጋችኹትን ነገር እናንተም እንዳለቆቻችሁ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን አስቀድሞ በነቢያት ሁሉ አፍ ‘መሲሑ መከራ መቀበል አለበት’ ያለው ቃል በዚህ ዐይነት እንዲፈጸም አደረገ። እንግዲህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስላችሁ ንስሓ ገብታችሁ ወደ ጌታ ተመለሱ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ የምትታደሱበት ዘመን ይመጣላችኋል፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን መሲሕ ኢየሱስን ይልክላችኋል።

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቅደስ ሊገቡ እንዳላቸው ባየ ጊዜ፥ ምጽዋትን ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ወደ እርሱ ተመልክቶ “ወደ እኛ ተመልከት፤” አለው። እርሱም አንድ ነገር ከእነርሱ እንዲቀበል ሲጠብቅ ወደ እነርሱ ተመለከተ። ጴጥሮስ ግን “ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ፤” አለው። በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጸና፤ ወደ ላይ ዘሎም ቆመ፤ ይመላለስም ጀመር፤ እየተመላለሰም እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ መቅደስ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፤ “መልካም” በሚሉአትም በመቅደስ ደጅ ስለ ምጽዋት ተቀምጦ የነበረው እርሱ እንደሆነ አወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መደነቅና መገረም ሞላባቸው። እርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዞ ሳለ፥ ሕዝቡ ሁሉ እየተደነቁ የሰሎሞን ደጅ መመላለሻ በሚባለው አብረው ወደ እነርሱ ሮጡ። ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በዚህ ስለምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኀይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሀምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቆርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው። እናንተ ግን ቅዱሱን ጻድቁንም ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩን ሰው ይሰጣችሁ ዘንድ ለመናችሁ፤ የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት፤ እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን። በስሙም በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን የእርሱ ስም አጸናው፤ በእርሱም በኩል የሆነው እምነት በሁላችሁ ፊት ይህን ፍጹም ጤና ሰጠው። “አሁንም፥ ወንድሞቼ ሆይ! እናንተ እንደ አለቆቻችሁ ደግሞ ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቄአለሁ፤ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራ እንዲቀበል አስቀድሞም በነቢያት ሁሉ አፍ የተናገረውን እንዲሁ ፈጸመው። እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፥ ኀጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም።