ሐዋርያት ሥራ 3:1-20

ሐዋርያት ሥራ 3:1-20 NASV

አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ፣ ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር። ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤ እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው። ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋራ ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስኪ ወደ እኛ ተመልከት!” አለው። ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት ዐስቦ በትኵረት ተመለከታቸው። ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤ ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቍርጭምጭሚቱ በረታ፤ ዘልሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋራ ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ። ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣ ይህ ሰው ቀደም ሲል “ውብ” በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ። የተፈወሰውም ሰው ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋራ ጥብቅ ብሎ ዐብሯቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደ ነበሩበት “የሰሎሞን መመላለሻ” ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ። ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቍጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ? የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በርሱ ፊት ካዳችሁት፤ ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤ የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን። ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው። “አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደ ሆነ ዐውቃለሁ። እግዚአብሔር ግን የርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሟል። እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን፣ እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል።